የሠራተኞችና አሰሪዎች የተቀናጀ ዕቅድና አፈጻጸል ለኢንዱስትሪ ሰላምና ምርታማነት ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ

65
መቀሌ ሚያዝያ 23/2010 የሠራተኞችና አሰሪዎች የተቀናጀ እቅድና አፈጻጸም ለኢንዱስትሪ ሰላምና ምርታማነት ወሳኝ መሆኑን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ታደለች ዳልቾ ገለጹ። በመቀሌ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአሰሪና ሠራተኞች ኮንፍረንስ ዛሬ ተጠናቋል። ሚኒስትሯ ወይዘሮ ታደለች በኮንፍረንሱ መዝጊያ ላይ እንዳሉት በማምረቻ ዘርፍ ይሁን በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተቀጠሩ ሠራተኞች  መብታቸው እንዲከበር በቅድሚያ የመደራጀት ህገ መንግስታዊ መብት ሊከበርላቸው ይገባል። "ሰራተኞች መብታቸውን ማስከበር የሚችሉት በመደራጀታቸው ብቻ ሳይሆን የተጣለበቸውን የሥራ ኃላፊነት ሲወጡ ጭምር እንደሆነም መገንዘብ ይገባቸዋል" ብለዋል። ሠራተኛውን በየደረጃው ያሳተፈ ዕቅድ መኖር አፈጻጸምን ስኬታማ ከማድረግ ባለፈ ለኢንዱስትሪ ሰላምና ምርታማነት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው  ተናግረዋል። በትግራይ ክልል ከአነስተኛ እስከ ከፍትኛ ያሉ የማምረቻና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ከ82 ሺህ በላይ ሠራተኛ መያዛቸውን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ኪሮስ ሐጎስ ናቸው። ከሠራተኞቹ መካከል ከ34ሺህ የሚበልጡት ሴት ሠራተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህ ሠራተኞች መካከል ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት የመደራጀት መብታቸውን ያስከበሩ 900 ብቻ መሆናቸውን አመልክተዋል። "ሠራተኞች ቀጣይነት ባለው መልኩ መብታቸውን ለማስከበርና የመደራደር አቅማቸውን ለማጎልበት በማህበር ሊደራጁ ይገባል" ብለዋል። ሰራተኛው ያሳተፈ ዕቅድ ከማውጣት ጀምሮ ከአሰሪዎች ጋር በቅርበት ተቀናጅቶ መስራት በስራ ላይ ስኬታማ ለመሆን ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል። በኮንፈረንሱ ታሳታፊ ከነበሩት ሠራተኞች መካከል በመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ የቴክኒክ ባለሙያ ወጣት ዙፋን ገብረህይወት አንዷ ናት። ወጣትዋ እንደገለጸችው መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ  የተሻለ ደመወዝ በመክፈልና የሰራተኛን ደህንነትን በመጠበቅ ሊጠቀስ የሚችል ተቋም ነው። በሠራተኞች የሚስተዋለው የሥራ ሰዓት አለማክበርና ተግቶ አለመስራት በቀጣይ መስተካከል እንዳለበት የተናገረችው ደግሞ በመሰብ ጨው አምራች ድርጅት እንደምትሰራ የተናገረችው ወጣት መድኃኒት  ገብረአነንያ ናት። በሥራ ላይ ስኬታማ ውጤት ለማስመዝገብ የአሰሪና ሠራተኛ ተግባብቶና ተቀራርቦ መስራው ወሳኝ መሆኑን አመልክታለች። ለሁለት ቀናት በተካሄደው የሠራተኞችና አሰሪዎች ኮንፍረንስ ከ600 በላይ ሰዎች ተሳታፊ ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም