ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አሰራሩን ለማዘመን መቸገሩን ገለጸ

261
ሰኔ 8/2011 በኢትዮ ቴልኮም በኩል አስፈላጊው ትብብር ስላልተደረገለትና በሌሎች ተያያዥ ችግሮች ምክንያት የሽያጭ ስርዓቱን ማዘመን እንዳልቻለ የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ገልጿል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ ብሄራዊ ሎተሪ ያቀረበውን ጥያቄ አለመከልከሉንና  አገልግሎቱን  ያለ ክፍያ በነጻ ማግኘት አለብኝ በማለቱ እንዳልተስማሙ ጠቁሟል፡፡ የአስተዳደሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ንዋይ ስለ ጉዳዩ በሰጡት ማብራሪያ የሎተሪ ሽያጭን በኤስኤምኤስ (አጭር መልዕክት) ለማካሄድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞችን ማፍራት ያስፈልጋል። ይህን ለማሳካት በተደጋጋሚ መልዕክት መላክን የሚጠይቅ ቢሆንም በኢትዮ ቴልኮም በኩል ከአንድ  ጊዜ በላይ ባለመፈቀዱ፤  በተደጋጋሚ ለመላክ ከፍተኛ ወጭን የሚጠይቅ በመሆኑ ሥራውን አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል። አሰራሩን ማዘመን ቢቻል በከተሞች አካባቢ የተወሰነውን የሎተሪ ሽያጭ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በማስፋፋት፤ የሎተሪ ጨዋታውንም በተሻለ ፍጥነት ለማካሄድ ያስችላልም ነው ያሉት። የአጭር መልዕክት  የሎተሪ ሽያጭ  ዘዴ ቀጥታ ከደንበኞች ጋር ስለሚያገናኝ በአሰራር ሂደቱ የሚታየውን አላስፈላጊ ወጭ ለማስቀረት እንደሚያስችል ጠቅሰዋል። አሰራሩ ዘመናዊ ቢሆን ወጪን በመቀነስ ለባለ እድለኞች የሚከፈለውን የሽልማት መጠን ለመጨመር ያስችላል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ከዓመታዊ ገቢው 6 በመቶው  ለህትመት ወጪ ሲሆን፤ ይህ በአማካይ ከ60 እስከ 70 ሚሊየን ብር  እንደሚደርስ ተናግረዋል። በ2001 ዓ.ም የሎተሪ ሽያጭን በኦን ላንይን ለማጫወት እንቅስቃሴ እንደነበረና ቴክኖሎጂውን ለማስገባት አቅም ስለሚጠይቅ በጆይንት ቬንቸር/በአክሲሆን/ ከሌላ ሀገር ድርጅት ጋር ለመስራት ጨረታ ወጥቶ ሀገሪቱ አሰራሩን ለመተግበር የሚያስችል የውል ስምምነት ስለሌላት መቋረጡንም ጠቁመዋል፡፡ የጆይንት ቬንቸር ቴክኖሎጂ የሞባይል ቀፎ በሚመስል ማሽን አማካኝነት ደንበኛው እራሱ ቁጥሮችን መርጦ የሚጫወትበት አሰራር እንደሆነም ነው ያብራሩት። ከአስር አመታት በፊት በሌሎች ሀገሮች እንደሚደረገው ሽያጩን በሱፐር ማርኬት፣ በግሮ ሰሪና በማንኛውም ሱቅ ለማድረግ ሁለት ተከታታይ አመታት ተሞከሮ ህብረተሰቡ  ልምዱ ስላልነበረው ውጤታማ ባለመሆኑ መቆሙንም ተናግረዋል። ኤስ ኤምኤስ የሎተሪ ሽያጭ አገልግሎት ላይ ቢውል ወጪን በመቀነስ እስካሁን ብዙ ገቢ መሰብሰብ ይቻል ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አልፎ አልፎ የሚታየውን ማጭበርበር ለማስቀረትም ይረዳል ሲሉ ነው የጠቀሱት። ምንም እንኳን አሰራሩ  ዘመናዊ ቢሆንም ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ አንጻር ሲታይ፤ ጎን ለጎን ከመጠቀም ውጪ የህትመት ሎተሪን ሙሉ ለሙሉ ማሰቀረት እንደማይቻልም ገልጸዋል። በኢትዮ ቴሌኮም የዋና ስራ አስፈጻሚ ቢሮ የጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሪት ጨረር አክሊሉ  በብሔራዊ  ሎተሪ  አስተዳደር  የቀረበውን ቅሬታ አስመልክተው በሰጡት ምላሽ፤ ለማህበራዊ ግልጋሎትና ለሰብአዊ እርዳታ ካልሆነ በስተቀር ገቢ ለመሰብሰብ ለሚሰራ ተቋም የነጻ አገልግሎት እንደማይሰጥ ተናግረዋል፡፡ የአገልግሎቱ ክፍያ  እየፈጸሙ የአጭር መልእክት የሚጠቀሙ ተቋማት እንዳሉ የጠቆሙት ሃላፊዋ፤ ብሄራዊ ሎተሪም አገልግሎቱን ለማግኘት አሰራር የሚፈቅደውን  ክፍያ መፈጸም እንደሚጠበቅበት ነው የተናገሩት። በሀገር አቀፍ ደረጃ አስር ሺህ ያህል የሎተሪ አዟሪዎች በሎተሪ ሽያጭ እየተሳተፉ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ ተቋሙ በዓመት ለሎተሪ አዟሪዎችና አከፋፋዮች በአማካይ እስከ 150 ሚሊዮን ብር ይከፍላል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም