በቆሻሻ አወጋገድ ላይ የተቀመጠው ህግ በአግባቡ እንዲተገበር የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ

75
ሰኔ 8/2011 በአሶሳ ከተማ ለጤና ስጋት እየሆነ የመጣውን የህብረተሰቡን የቆሻሻ አወጋገድ ለማሻሻል በቆሻሻ አወጋገድ ላይ የተቀመጠው ህግ በአግባቡ እንዲተገበር ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡ በአሶሳ ከተማ ለጤና ስጋት እየሆነ የመጣውን የቆሻሻ አወጋገድ ለማሻሻል በቆሻሻ አወጋድ ላይ የተቀመጠው ህግ በአግባቡ እንዲተገበር ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡ በአሶሳ ከተማ በተከበረው የዓለም የአካባቢ ቀን በዓል ላይ የተሳተፉ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎች የከተማዋን ጎዳናዎችና ፍሳሽ መውረጃ ትቦዎችን ከቆሻሻ አጽድተዋል፡፡ በጽዳት ሥራው ከተሳተፉት መካከል ወይዘሮ ደጊቱ አራርሳ እንዳሉት በከተማው ጨለማን ተገን በማድረግ የሚጣለው ቆሻሻ ከጊዜ ወደጊዜ እየተበራከ የመጣ ሲሆን የጤና ስጋትም ሆኗል። የከተማው የፍሳሽ ቆሻሻ መውረጃ ትቦዎች ከመኖሪያ ቤት እና ከንግድ ተቋማት በሚወጡ ፕላስቲክ ጠርሙሶች፣ የጫት ገራባዎችና ሌሎች ቆሻሻዎች ተሞልተው አስፓልቱ በጎርፍ የሚጥለቀለቅበት ሁኔታ መኖሩንም ተናግረዋል። በተለይም አውቶብስ ተራ በተባለው የከተማው አካባቢ ችግሩ ጎልቶ እንደሚታይ አስተያየት ሰጪዋ ገልጸዋል፡፡ ቆሻሻን ያለአግባብ መጣል የሚያስቀጣ በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ቆሻሻን በግዴለሽነት በየቦታው በሚጥሉ ግለሰቦች ላይ ህጉን መሰረት ያደረገ ተገቢ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎችም የመኖሪያ ግቢ ቆሻሻቸውን በአግባቡ በማስወገድ ለከተማዋ ጽዳት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ነው የገለጹት። አቶ በሽር ሙስጣፋ የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው የአካባቢ ንጽህና አለመጠበቅ ጉዳቱ ለራስ ከመሆን ባለፈ በእስልምና ሃይማኖትም እንደማይደገፍ ተናግረዋል፡፡ “ማህበረሰቡ አካባቢን ማጽዳት ያለበት በዓላትንና ወራዊ የጽዳት ዘመቻዎችን ጠብቆ ሳይሆን የዕለት ተዕለት ተግባሩ በማድረግ ሊሆን ይገባል” ብለዋል። አቶ በሽር እንዳሉት ከተማን የማስዋብ ሥራ የመንግስት ኃላፊነት ብቻ ተደርጎ መወሰዱ ለከተማው ቆሻሻ መበራከት አንድ ምክንያት ነው። “ህብረተሰቡ የጽዳት ሥራው የሌላ አካል ነው በሚል ጠባቂ ከመሆን ይልቅ ለአካባቢ ጽዳት ቅድሚያ መስጠት ይኖርበታል” ሲሉም ገልጸዋል። በአሶሳ ከተማ እየተስተዋለ ያለውን የቆሻሻ አወጋገድ ችግር የጤና ስጋት እየፈጠረባቸው በመሆኑ ይህን ለማሻሻል የከተማው አስተዳደር በቆሻሻ አወጋገድ ላይ የተቀመጠው ህግ በአግባቡ ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠይቀዋል። የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ የሆኑት አቶ መሀመድ ኡስማን በቡኩላቸው ቆሻሻ የገቢ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ህብረተሰቡን ማስተማር አካባቢን ለማጽዳት ቀላሉ ዘዴ መሆኑን መክረዋል፡፡ “በአሶሳ ከተማ በቆሻሻ አወጋገድ ላይ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ቆሻሻቸውን ያለአግባብ በሚጥሉ ግለሰቦች ላይ በገንዘብ በማስቀጣት እርምጃ ተወስዷል” ያሉት ደግሞ በአሶሳ ከተማ አስተዳደር የወረዳ 1 ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ መሀመድ ኢብራሂም ናቸው፡፡ አሁንም ቆሻሻቸውን በግዴለሽነት የሚጥሉ ግለሰቦች መኖራቸውን የተናገሩት አቶ መሀመድ ከቆሻሻ አወጋገድ ጋር በተያያዘ በአስተዳደሩ በኩል የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ አስተዳደሩ በቀጣይ የሌሎች ከተሞችን ተሞክሮ በመውሰድ ከተማዋን ከቆሻሻ የነጻችና ለኑሮ ምቹ የማድረግ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ ከተማዋን በማጽዳት ሥራ ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣም አቶ መሀመድ ጥሪ አቅርበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም