የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ የህዝብ ዓይንና ጆሮ ሆኖ እንዲያገለግል ድጋፍ ይደረጋል....አቶ ሽመልስ አብዲሳ

76
ሰኔ 7/2011 የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦ.ቢ.ኤን ) የተለያዩ አስተሳሰቦችን በእኩል እንዲያስተናግድና የህዝብ ዓይንና ጆሮ ሆኖ እንዲያገለግል የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ። ለኦ.ቢ.ኤን የባሌ ኤፍ.ኤም ሬድዮና ቴሌቪዥን ስርጭት የሚሆን ስቱዲዮ ግንባታ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት በተገኙበት ዛሬ በባሌ ሮቤ ከተማ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል። ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ሽመልስ የመሰረት ድንጋዩን ሲያስቀምጡ እንደተናገሩት ድርጅቱ የተለያዩ አስተሳሰቦችን በዲሞክራሲያዊ መልኩ የሚያስተናገድበትና ህዝቡን ለልማት የሚያነሳሳ የሚዲያ ተቋም እንዲሆን የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው። “በተለይ ወቅቱ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ በመታጠቅ የህዝቡ ዓይንና ጆሮ ሆኖ እንዲያገለግል ለሚዲያ መሰረተ ልማት እና ለሰው ኃይል የአቅም ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል” ብለዋል። የኦ.ቢ.ኤን የኢንጂነሪግ ዘርፍ ኃላፊና የድርጅቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጅማ ቱሉ በበኩላቸው ድርጅቱ የማህበረተሰቡን የመረጃ ፍላጎት ለማሟላት ለመሰረተ ልማት ዝርጋታና ለባለሙያ አቅም ግንባታ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል። መረጃን በአግባቡና በጥራት አድማጭ ተመልካቹ ጋር ተደራሽ ለማድረግ ድርጅቱ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ በባሌ ዞን ዘመናዊ ሚዲያ ያሟላ ስቱዲዮ ለማስገንባት ዛሬ የተቀመጠው የመሰረት ድንጋይ የእዚህ አካል መሆኑንም አስረድተዋል። ኦ.ቢ.ኤን በባሌ ዞን የሚገነባውን ዘመናዊ ስቲዲዮ ጨምሮ በሌሎች አራት የክልል ዞኖች ውስጥ ለኤፍ.ኤም ሬድዮ ስርጭትና ለዘመናዊ የተሌቪዥን ስቲዲዮ ግንባታ የሚውል መሰረተ ልማቶችን እያካሄደ መሆኑን በማሳያነት አቅርበዋል። ባለፈው ግንቦት ወር በሙከራ ደረጃ  ስርጭቱን የጀመረው የባሌ ኤፍ.ኤም 96 ነጥብ 5 ሬድዮ ጣቢያ በባሌ ዞን ጎባና ሮቤን ጨምሮ በ100 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎችን ተደራሽ ያደርጋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም