የወሎ ኮምቦልቻ ስፖርት ቡድንን ለማጠናከር የተዘጋጀ ባዛር ተከፈተ

119
ሰኔ 7/2011 የወሎ ኮምቦልቻ ስፖርት ቡድንን ማጠናከር ዓላማው ያደረገ አገር አቀፍ ባዛር በኮምቦልቻ ከተማ ተከፈተ። የባዛሩ አስተባባሪ አቶ አብዱ ኢሊ እንደተናገሩት የወሎ ኮምቦልቻ እግር ኳስ ቡድን ከብሔራዊ ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ ቢሸጋገርም በገንዘብ እጥረት ምክንያት የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አልቻለም። የቡድኑን የገንዘብ ችገር ለመፍታት ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሰኔ15 ቀን 2011 ዓ.ም የሚቆይ አገር አቀፍ የንግድ ባዛር መዘጋጀቱን ገልፀዋል። በባዛሩ 150 አገር አቀፍ ነጋዴዎች እንዲሳተፉ በማድረግ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱንም አስተድረዋል። የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ ዶክተር ከማል መሀመድ በበኩላቸው “ከተማ አስተዳደሩ የቡድኑን ወጪ ቢሸፍንም በበጀት እጥረት ምክንያት የሚያስፈልገውን ሁሉ ማሟላት አልተቻለም” ብለዋል። የተለያዩ የገቢ አማራጮችን በመጠቀም ቡድኑን ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል። ባዛሩ የከተማውን የንግድ እንቅስቃሴ ከማነቃቃቱ በተጨማሪ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ከተሳታፊ ነጋዴዎች መካከል ከደሴ ከተማ የመጡት ወይዘሮ ሰሚራ አህመድ የተለያዩ የወንድና የሴት ልብሶችን ይዘው በባዛሩ ላይ መቅረባቸውን ገልጸዋል። በባዛሩ ቆይታቸው ጥራት ያላቸው ልብሶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በመሸጥ የተሻለ ትርፍ ለማግኘት ማቀዳቸውንም ተናግረዋል። ከዚህ በፊት በከተማው በተካሄዱ ባዛሮች በመሳተፍ ተጠቃሚ እንደነበሩም አስታውሰዋል። በኮምቦልቻ ከተማ ቀበሌ 05 የሚኖሩት አቶ የሱፍ ጀማል በበኩላቸው በኮምቦልቻ ከተማ በቀላሉ የማይገኙ እቃዎችን ለመግዛት ባዛሩ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል። የወሎ ኮምቦልቻ እግር ኳስ ቡድን በከፍተኛ ሊጉ ካሉ 12 ቡድኖች ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም