የብዝሃ ህይወት ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል

74
ጎባ ሰኔ 1/2010 የብዘሃ ሕይወት ሀብትን  በዘላቂነት ለመጠቀም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ብዝኀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ጥሪ አቀረበ ። በአገሪቱ  ለ17ኛ ጊዜ  እየተከበረ ያለው የብዝኀ ሕይወት ቀን በዞን ደረጃ ትናንት በባሌ ጎባ ከተማ በተለያዩ ፕሮግራሞች ተከብሯል፡፡ በበዓሉ ላይ የተገኙት በኢንስቲትዩቱ የጎባ ብዘኀ ህይወት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ግርማ እንደተናገሩት የበዓሉ መከበር ማኅበረሰቡ ስለብዝኀ ሕይወት ያለው ግንዛቤ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ''በተለይ በትምህርት ቤቶች መከበሩ አዲሱ ትውልድ የብዘኀ ሕይወት ሀብትን መጠበቅና በዘላቂነት መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስችላል'' ብለዋል፡፡ አቶ ንጉሱ እንዳሉት በብዝኀ ሕይወት ዙሪያ በሁሉም ሕብረተሰብ ዘንድ ግንዛቤ መፈጠሩ አሉታዊ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ ፣ ለስነ ምህዳር ፈታኝ የሆነውን መጤ ዝርያ ለመግታት አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳሉት ማእከሉ የብዘኀ ህይወት ሀብት ተጠብቆ በዘላቂነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ከመስራት በተጓዳኝ በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በጥናት ለመለየት መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ማዕከሉ በዘንድሮው ዓመት ከ2ሺህ የሚበልጡ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸው ሀገር በቀል ችግኞችን ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች በማሰራጨት መተከላቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህንኑ የብዝሃ ህይወት ሀብት በተቀናጀና በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው ርብርብ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል ። ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል የቱሉ ዲምቱ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ታምሩ ወጨኖ  በሰጡት አስተያየት ''በዓሉ በትምህርት ቤቶች መከበሩ ወጣቱ ትውልድ ስለብዘኀ ህይወት ግንዛቤ ኖሮት በጥበቃውም ላይ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ያስችላል'' ብለዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን በብዘኀ ህይወት ክለብ በማደራጀት ከራሳቸው አልፈው ለሌላው ማህበረሰብ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ መሐመድ ጃርሶ በበኩሉ “ በትምህርት ቤታቸው በብዝሃ ህይወት ክለብ በመሳተፍ  የቀሰመው እውቀት  ግንዛቤውን እያሳደገ እንዲመጣ እንዳገዘው ተናግሯል፡፡ በበዓሉ ላይ ከትምህርት ቤቶቹ ማህበረሰብ  ባሻገር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ላይ ከብዘሃ ህይወት ጋር የተገናኘ ድራማ፣ የጥያቄና መልስ ውድድርን ጨምሮ  የችግኝ ተከላ ተካሄዷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም