የኤች አይቪ/ኤድስ ስርጭት ወረርሽኝ የሆነባቸው አካባቢዎች ከወረርሽኙ ለመውጣት እየሰራን ነው አሉ

84
ሰኔ 7/2011 በኢትዮጵያ የኤች. አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት ወደ ወረርሽኝ በተሸጋገረባቸው ጋምቤላና አዲስ አበባ ከተሞች ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ። በዓለም አቀፍ የወረርሽኝ መለኪያ መስፈርት መሰረት አንድ በሽታ ስርጭቱ ከአንድ በመቶ በላይ ከሆነ በሽታው ወደ ወረርሽኝ አድጓል ይባላል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለው አጠቃላይ የኤች.አይ. ቪስርጭት ግን 0 ነጥብ 9 በመቶ ነው። ይሁን እንጂ የበሽታው ስርጭት በእድሜ፣ በክልል፣ በከተማ፣ በጾታ የተለየያ መጠን ያለው በመሆኑ በተለይ በአዲስ አበባ እና ጋምቤላ ክልል የበሽታው ስርጭት ከአንድ በመቶ በላይ ማደጉን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጣሪያ ጽህፈት ቤት መረጃ ያሳያል። በዚህም መሰረት ጋምቤላ በ4 ነጥብ 3 በመቶ፣ አዲስ አበባ 3 ነጥብ 6 በመቶ ድሬዳዋ 2 ነጥብ 3 በመቶ በመሆን በእነዚህ አካባቢዎች ያለው የቫይረሱ ስርጭት ወደ ወረርሽኝ ማደጉም ተመልክቷል። የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ላፊ አቶ ካን ጋልሞክ ለኢዜአ እንደተናገሩት በክልሉ በሽታው ወደወረርሽኝነት እንዲሸጋገር የተለያዩ አባባሽ ምክንያቶች አሉ። ከነዚህም ውስጥ የግንዛቤ ማነስ፣ የውርስ ጋብቻ፣ መጤ ባህሎች፣ የኢንቨስትመንት መስፋፋት፣ ኮንዶም አለመጠቀምና ሌሎችን ይጠቅሳሉ። ስርጭቱን ለመቀነስ የኤድስ ምክር ቤትን በክልል ደረጃ በማጠናከ ከአመራሩ ጀምሮ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት በመቀየር ለህብረተሰቡ ስለበሽታው አስከፊነት የግንዛቤ በማስፋት ከወረርሽኝ ለመውጣት እየሰሩ መሆኑን ኃላፊው ይናገራሉ። በስርጭት ምጣኔ በሁለተኛ ደረጃ የምትገኘው አዲስ አበባም አንድ መቶ ዘጠኝ ሽህ ነዋሪዎቿ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ የከተማዋ ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት መረጃ ያሳያል። የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ሲስተር ብሪዛብ ገብሩ የልማት፣ቱሪዝምና መዝናኛ ቦታዎች መስፋፋት በሽታው ወረርሽኝ እንዲሆን አስተዋጽኦ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ይላሉ። በተጨማሪም የራቁት ዳንስ ቤቶች፣ መጤ ባህሎች፣ የግንዛቤ ማነስ፣ የመዝናኛ ቦታዎችና ሌሎችም የበሽታው አባባሽ ሁኔታዎች ሲሆኑ ወጣቱና ሴቶች ለበሽታው ተጋላጭ እንደሆኑ በጥናት መለየታቸውን ተናግረዋል። አሁን ባለው 3 ነጥብ 6 የስርጭት ምጣኔ 62 በመቶ ሴቶችና 90 በመቶ ወጣቶች ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው። አምራቹና የነገ አገር ተረካቢው ወጣት በከፍተኛ ሁኔታ ለበሽታው ተጋላጭ መሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል። እንደ ሃላፊዋ ገለጻ በተደረገው የጥናት ውጤት መሰረትና የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ከወረርሽኝ ለመውጣት እስትራቴጂ ተቀርጾ እየተሰራ ነው። የፌደራል ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ዋና ዳሬክተር ዶክተር ጽጌሬዳ ክፍሌ በበኩላቸው ጋምቤላ፣ አዲስ አበባ፣ድሬዳዋና ሃረር እንደ አገር ካለው የስርጭት ምጣኔ አንጻር በወረርሽኝ መልክ የሚያስፈራ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል። በእነዚሀ ከተሞች በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ተብለው የተለዩ ሴተኛ አዳሪዎች፣ ተንቀሳቃሽ ሰራተኞች፣ ከገጠር ወደከተማ የህዝብ ፍልሰት ከፍተኛ መሆን ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል ይላሉ። በመሆኑም በእነዚህ ክልሎች በተቀናጀ ሁኔታ ተጋላጭ ተኮር ስራዎች ላይ በተለየ ሁኔታ መሰራት እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ በኢትዮጵያ እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር በ2018 መረጃ መሰረት ከ610 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቫይረስ ጋር ይኖራሉ። በተመሳሳይ ከ13 ሺህ በላይ ሰዎች በአንድ አመት በበሽታው ህይወታቸውን እንደሚያጡም ተተንብዮዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም