ብሔራዊ ፓርኮች ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባቸዋል

143
ሰኔ 7 /2011 በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች ከፍተኛ አደጋ የተጋረጠባቸው መሆኑን የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ። በብሔራዊ ፓርኮቹ ላይ የተጋረጠውን ስጋት ለማስወገድ ፓርኮች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ባለስልጣኑ ገልጿል። በባለስልጣኑ የብሔራዊ ፓርኮችና መጠለያዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ገብረመስቀል ግዛው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በፓርኮች ላይ ስለተደቀነው አደጋ በስፋት መነገር ከጀመረ ሁለት ዓመት አልፏል። በፓርኮች ውስጥ የሚካሄድ ሰፈራ ችግሩን የከፋ እንዳደረገው የገለጹት አቶ ገብረመስቀል፤ የባሌ ብሔራዊ ፓርክና አብያታ ፓርክ የችግሩ ዋነኛ ሰለባ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በነዚህ ፓርኮች ውስጥ ሰፍረው የሚገኙ ሰዎችን ከፓርኩ ለማስወጣትና በሌላ ስፍራ ለማስፈር ባለስልጣኑ የተለያዩ አካላት ድጋፍ የሚያስፈልገው መሆኑንም ተናግረዋል። ከሰፈራ ባለፈ ፓርኮች ለግጦሽ መዋል፣ ለእርሻ አገልግሎት መዋልና የእሳት አደጋ ተጋላጭ መሆን እየተባባሰ የመጣ የፓርኮች ችግር መሆኑን ተናግረዋል። በፓርኮች ውስጥ የሚከሰተው የእሳት አደጋ ከስነምህዳር ጋር የተያያዘ በመሆኑ የከፋ ስጋት እንዳልሆነ ገልጸው ሰፈራ፣ ግጦሽ፣ እርሻና የማዕድን ማውጣት ተግባር ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ችግር መሆኑን አመልክተዋል። እንደ አቶ ገብረመስቀል ገለጻ፤ በፓርኮቹ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመፍታት ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲይዛቸው ማድረግ ያስፈልጋል። ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ጥረቶች ቢኖሩም የሚፈለገውንያህል እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ ህብረተሰቡን ከፓርኮቹ ተጠቃሚ ለማድረግ የቱሪስት ተደራሽነትን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ገብረመስቀል፤ ቱሪስቶች የሚጎበኙ ፓርኮች አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች የቱሪስት አገልግሎት በመስጠት እየተጠቀሙ እንደሆነ ተናግረዋል። ይህም ቢሆን ግን በቱሪስቶች እየተጎበኙ ያሉ ፓርኮች ውስን በመሆናቸው የሚፈለገውን ያህል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ አለመቻሉን ገልጸዋል። በዘላቂነት በፓርኮች አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረ የሚያስችል የመተማመኛ የገንዘብ ቋት ለመመስረት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም