የምርጫ ቦርድ ስራ አመራር አባላት ሹመት ጸደቀ

64
ሰኔ 6/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 44ኛ መደበኛ ስብሰባ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርድ አባላት ሹመትን ጨምሮ ስድስት ረቂቅ አዋጆችን ነው ያጸደቀው። ምክር ቤቱ ምርጫ ቦርዱን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 5 መሰረት ወይዘሮ ብዙወርቅ ከተተ፣ አቶ ውብሸት አየለ፣ ዶክተር ጌታሁን ካሳ እና አቶ አበራ ደገፉ የቦርዱ ስራ አመራር አባላት ሆነው እንዲሾሙ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ የአባላቱን ሹመት አጽድቋል። በአዋጁ መሰረት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው የሚቀጥሉ ሲሆን አቶ ውብሸት አየለ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ያገለግላሉ። ሹመታቸው በምክር ቤቱ የጸደቀው አባላት በቂ የትምህርት ዝግጅትና የሙያ ስብጥር ያላቸው ተፈላጊውን መስፈርት ያሟሉ መሆናቸው ነው የተገለጸው። የቦርዱ ስራ አመራሮች ሹመት በ17 ተቃውሞና በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል። ምክር ቤቱ በዛሬው ስብሰባ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 16 ዕጩ ዳኞች ሹመትንና የፌዴራል ከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ዕጩ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሹመትንም አጽድቋል። ምክር ቤቱ ዛሬ ሹመታቸውን ያጸደቀው ዳኞች የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ጥራት ያላቸው፣ በዳኝነት ስራ ላይ ትጋትና ሀቀኝነት የሚያሳዩ በመሆናቸው በስነ ምግባራቸው የተመሰገኑ እንደሆነም ነው የተገለጸው። አቶ ብርሃነ መስቀል ዋቅጋሪ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ ወይዘሮ ተናኜ ጥላሁንና አቶ ተክሊት ይመስል ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሆነው በአንድ ተቃውሞ፣ በ10 ድምጸ-ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ተሹመዋል። አቶ ፉአድ ኪያር የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ ወይዘሮ አሸነፈች አበበ እና አቶ ተስፋዬ ነዋይ ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሆነው ተሾመዋል። ምክር ቤቱ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፣ ተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያለ የዋስትና መብት፣ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት እንዲሁም በመንግስትና በአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ መካከል የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረቡለትን ረቂቅ አዋጆችም መርምሮ አጽድቋል። በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የባንክ ስራ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም