የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመቆጣጣር ፈጣን ርብርብ ካልተደረገ የከፋ አደጋ ይፈጠራል - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ

71
ሰኔ 6/2011 በኢትዮጵያ በፈጣን ሁኔታ እንደገና እያንሰራራ የመጣውን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታ ስርጭት ለመግታት ከወዲሁ ፈጣን የጋራ ርብርው ካልተደረገ በሽታው በቀላሉ መመለስ ወደማይቻልበት ደረጃ ሊሸጋጋር ይችላል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አስጠነቀቁ። ፕሬዝዳንቷ ይህን ያሉት 14ኛ የኤች.አይ.ቪኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ አዲስ አበባ ውስጥ ሲካሄድ ነው። ከበሽታው መንሰራፋት ጋር ተያይዞከ20 ዓመታት በፊት በአገሪቱ የተከሰተው አስፈሪ ሁኔታ አሁንም ተመልሶ እያገረሸ መሆኑን ፕሬዚዳንቷ ለምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል። እንዲያውምበአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በሽታው ወደወረርሽኝ ደረጃ ሊያሸጋገር እንደሚችል ነው የቅርብ ጊዜ ጥናትን ዋቢ በማድረግ ያስጠነቀቁት። በሽታው ከህመም አልፎ የተወሳሰበ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በፍጥነት የሚያስከትል በመሆኑ ዜጎች በድህነት ውስጥ እንዲኖሩ ያስገድዳቸዋል ሲሉም ጨምረዋል። እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጣር በ2030 በኤድስ የመያዝን፣ከኤድስ ጋር ተያያዥ የሆነ ሞትን፣ በኤድስ የተነሳ የሚፈጠር መገለልን ዜሮ ለማድረስ የተያዘውን እቅድ አሁን ካለው የቸልተኝነት ካልተወጣ ማሳካት እንደማይቻል በአጽእኖት ተናግረዋል። በመሆኑም የሚያስከትለውን አዳዲስ ጉዳቶችና ቀውስ ለመቀነስ ቃል መግባት ብቻ ሳይሆን በተግባር አፋጣኝ መፍትሄ ያስፈልጋል ብለዋል። አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት ስንረባረብ በሽታው እቅዳችንን እንዳያጨናግፈው መስራት አለብን ሲሉም መክረዋል። የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ያስመዘገበችው ለውጥ መዘናጋት በመፍጠሩ በአሁኑ ወቅት ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል ይላሉ። በየደረጃው ያለው አመራርና የማህበረሰብ ክፍል ለበሽታው የሚገባውን ትኩረት አለማግኘትና አጋላጭ ሁኔታዎች እየተስፋፉ መምጣት ሁኔታውን አስጊ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። የፌደራል የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጽጌሬዳ ክፍሌ ደግሞ ባለፉት ዓመታት የበሽታውንስርጭት ከዋና አጀንዳ በማውጣት እንደተጨማሪ ስራ መቆጠሩ ለስርጭቱ መጨመር በምክንያትነት ያስቀምጣሉ። በመሆኑም በቀጣይ የክልል ኃፊዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የኤድስ ምክር ቤት እስከ ወረዳ በማቋቋም በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪኤድስ የስርጭት 0 ነጥብ 9 ምጣኔ ላይ ይገኛል። በስርጭት መጠንም ጋምቤላ በአንደኝነት የሚገኝ ሲሆን አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ በሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ናቸው። ስርጭቱ በከተማና በገጠር፣ በጾታ፣ በክልል እንዲሁም በእድሜ ልዩነት እንዳለው አንስተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በኤድስ በሽታ ምክንያት የሚከሰተው የሞት መጠን እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር 2004 83 ሺህ የነበረ ሲሆን በ2017 ግን የሞት መጠኑ ወደ ከ15 ሺህ ቀንሶ ነበር። ሆኖም በ2020 የሞት መጠኑ በ75 በመቶ በመቀነስ በ2030 የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት በትክክልኛው ፍጥነት ላይ እየሄደች አይደለም። የኤች.አይ.ቪኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት በ1994 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሰብሳቢነት የሚመራና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተሩን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ሃላፊዎችን በአባልነት የያዘ ነው። ስብሰባው ላለፉት 4 አመታት ሳይካሄድ የቆየ ሲሆን ዛሬ በተካሄደው ስብሰባ ቀዳማዊ እመቤትን ጨምሮ 7 አዳዲስ አባላት ተጨምረዋል። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅበዛሬው መርሃ ግብር የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ባለስድስት ነጥብ የቃልኪዳን ሰነድ ለክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች  አስረክበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም