የኢትዮጵያ ቡናና የመቐለ 70 እንደርታ እግር ኳስ ጨዋታ ለአራተኛ ጊዜ ተራዘመ

60
ሰኔ 7/2011 የኢትዮጵያ ቡናና የመቐለ 70 እንደርታ እግር ኳስ ጨዋታ በመጪው ማክስኞ በአዲስ አበባ ስታዲየም ደጋፊዎች በተገኙበት ይካሄዳል ተብሏል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው፤ የጸጥታ ሃይሉ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረጉ ጨዋታው የሁለቱም ክለቦች ደጋፊዎች በተገኙበት ይካሄዳል። ጨዋታውን በሰላም ለማካሄድ የጸጥታ አካላት፣ የሁለቱ ክለብ አመራሮችና ፌዴሬሽኑ በጋራ ውይይት ማድረጋቸውን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ገልጸዋል። በውይይቱም ከፀጥታ አካሉ በኩል ጨዋታው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና ከጨረሱ በኋላ የሁለቱም ደጋፊዎች በተገኙበት ጨዋታው ማካሄድ እንደሚቻል ገልጿል ብለዋል። እንዲሁም ጨዋታው ከመካሄዱ በፊት የሁለቱ ክለብ አመራሮች ጨዋታው በሰላም እንዲጠናቀቅ የጋራ ውይይት እንዲያካሄዱ የፀጥታ ሀይሉ በኩል መነገሩ  ተገልጿል። ይህን ተከተሎም ዛሬ ይካሄዳል ተብሎ የታሰበው የኢትዮጵያ ቡናና የመቐለ 70 እንደርታ እግር ኳስ ጨዋታ በመጪው ማክሰኞ ከቀኑ በ10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል። ግንቦት 25 ቀን 2011 ዓ.ም 27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፕሪሚሪሊግ ይካሄዳል የተባለው ይህ ጨዋታ በእለቱ ከፀጥታ ስጋት ጋር ተያይዞ መሰረዙ ይታወሳል። ከዚያ በኋላም ጨዋታው አዳማ ላይ በዝግ እንዲካሄድ የተወሰነ ሲሆን ይህ ጨዋታም እለቱ የኢድ አል-ፈጥር በዓል በመሆኑ በሚል በድጋሚ ከሁለት ቀናት በኋላ እንዲካሄድ ተወሰኖ ነበር። ይህን ጨዋታም ኢትዮጵያ ቡና በዝግ ስታዲየም መካሄዱንና የቦታ ለውጥ መደረጉን በመቃወሙ ጨዋታው አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ ተራዝሞ እንደነበር ይታወቃል። ጨዋታው ለሶስተኛ ጊዜ ሲራዘም ቦታው አዲስ አበባ ስታዲየም ይሁን እንጂ በዝግ እንዲካሄድ ነበር የተገለጸው። ዛሬ በዝግ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲካሄድ ተወስኖ የነበረው ይህ ጨዋታ አሁንም በድጋሚ ለአራተኛ ጊዜ ተራዝሞ የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ክፍት ሆኖ በመጪው ማክሰኞ እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም