በሃላባ ዞን ቁሊቶ ከተማ የሰላምና የእርቅ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው

48
ሰኔ 7/2011 በሀላባ ዞን ቁሊቶ ከተማ ባለፈው የካቲት ወር መጀመሪያ ተከስቶ በነበረ ግርግር የተፈጠረውን ቅራኔ በሰላም ለመፍታት ዛሬ የሰላምና የእርቅ ኮንፈረንስ በከተማዋ መካሄድ ጀመረ። “የእምነት ተቋማትን በጋራ የገነባ ህዝብ ጥቂት ተንኳሾች ሊለያዩት አይችሉም” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ባለው የሰላምና የእርቅ ኮንፈረንስ ላይ ከዞን፣ ከክልልና ከፌደራል የመጡ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል። በእስልምናና በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በተሳሳተ ምክንያት ተከስቶ በነበረ አለመግባባት የተፈጠረውን ቅራኔ ለመፍታት የሚያስችል የህዝብ ለህዘብ ሰላም በዘላቂነት ለማስፈን ታስቦ ውይይቱ መዘጋጀቱን የኮንፈረነሱ አዘጋጆች ተናግረዋል። ባለፈው የካቲት 2 ቀን 2011 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው ችግር ተቃጥለው የነበሩ ሰባት የፕሮቴስታንት እምነት አብያተክርስቲያንት ውስጥ አራቱ ህብረተሰቡ ባዋጣው 500 ሺህ ብር ጥገና ተደርጎላቸው ወደአገልግሎት መግባታቸው ታውቋል። ቀሪዎቹን አብያተክርስቲያናት ሥራ ለማስጀመር የቁሳቁስና የገንዘብ መዋጮ በህብረተሰቡ በኩል እየተደረገ መሆኑንም አስተባባሪው አመልክተዋል። ዛሬ እየተካሄደ ባለው ኮንፈረንስ ላይ የሁለቱም አምንት ተከታዮች በቀጣይ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ በመምከር ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም