በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ነገ ይጀምራል

139
ሰኔ 5/2011 በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል ተከስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ ለጥቂት ቀናት ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ነገ እንደሚጀምር የዩኒቨርሲቲው ሴኔት አስታወቀ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር ደረጄ አንድአርጌ እንደገለጹት ከውጭ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው በሚንቀሳቀሱና መማር በማይፈልጉ ጥቂት ተማሪዎች ተቀስቅሶ በነበረ ግጭት በንብረት ላይ ውድመት፤ በተማሪዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሷል። በእዚህ ምክንያት በዩኒቨርሲቲው ትምህርት ለጥቂት ቀናት መቋረጡንና ትናንት የሀገር ሽማግሌዎችና ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በተገኙበት ከተማሪዎች ጋር በተደረገ ውይይት የተቋረጠውን ትምህርት ለመጀመር መግባባት ላይ መደረሱን አስረድተዋል። ይህን ተከትሎም የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በተቋሙ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት በተማሪዎች ላይ የደረሰውን የስነልቦና ጫና በመገምገም ተማሪዎች በትምህርት ክፍላቸው አማካኝነት አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ወስኗል። ከነገ ሰኔ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት ክፍላቸው አማካኝነት በሚሰጠው የማካካሻ ትምህርትም ሁሉም ተማሪዎች በትምህርት ገባታቸው ላይ ተገኝተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አመልክተዋል። የተመራቂ ተማሪዎች የማጠቃለያ ፈተና ከሰኔ 13 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሰጥ፤ ሌሎች ተማሪዎች ደግሞ ከሰኔ 17 ቀን ጀምሮ ዓመታዊ ፈተናውን እንደሚወስዱም ገልፀዋል። የእዚህ ዓመት የተማሪዎች መመረቂያ ጊዜም ተሻሽሎ ሐምሌ 6 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲሆን በሴኔቱ መወሰኑን የገለጹት ዶክተር ደረጀ፣ ተማሪዎች ይህን አውቀው ከነገ ጀምሮ በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ ጥሪ አቅርበዋል። ዶክተር ደረጄ አያይዘው እንደገለጹት በግጭቱ ወቅት ንብረታችን ተሰረቀብን ለሚሉና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው የሚችለውን ድጋፍ ለማድረግ ኮሚቴ ተቋቁሟል። በዩኒቨርሲቲው የተከስተውን ግጭት አስመልክቶ ትናንት የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት በዩኒቨርሲቲው በተደረገ ውይይት በተማሪዎች መካከል እርቅ እንዲወርድ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም