የፈጠራ ባለሙያዎች የጀመሩትን ጥረት በመቀጠል ለበለጠ ውጤት መትጋት አለባቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

120
ሰኔ 5/2011  የፈጠራ ባለሙያዎችና ተማሪዎች ቀጣይነት ላለው የፈጠራ ስራ ትኩረት በመስጠት ለበለጠ ውጤት ሊተጉ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ። ዘጠነኛው አገር አቀፍ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ልማት ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት ዛሬ በአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ተጠናቋል። በመርሃ ግብሩ ላይ ከአጠቃላይ ትምህርት ተማሪዎችና መምህራን፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሰልጣኞችና አሰልጣኞች፣ የምርምርና የፈጠራ ባለሙያዎች በአጠቃላይ 194 ባለሙያዎች ላበረከቱት የላቀ የፈጠራ ሥራ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ከተሸላሚዎቹ መካከል ግብርንና፣ ጤናን፣ ኢንዱስትሪንና የተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች ላይ የተካሄዱ ጠቃሚ የምርምር ውጤቶችን ለተግባር ያበቁ ይገኙበታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድበመርሃ ግብሩ ማጠቃላያ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ የፈጠራ ስራን መጨረስ ማለት የሰዎችን ህይወት ሲቀይርና ሲነካ በመሆኑ የፈጠራ ባለሙያዎችና ተማሪዎች በጀመሯቸው የፈጠራ ስራዎች ሳይኩራሩና ሳይዘናጉ በትጋት በመስራት ለውጤት ማብቃት ይኖርባቸዋል። የፈጠራ ባለሙያዎች ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመሆን በጋራ፣ በትብብርና በመደመር በመስራት ፈጠራቸው እንዲጎለብት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ዶክተር አብይ ጠቁመዋል። መንግስት የፈጠራ ሥራዎችን ለማበረታታት በሚችለው አቅም ሁሉ የሚፈለግበትን ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል። የፈጠራ ስራቸውን ለዓለም ያበረከቱ እና በአርያነት የሚጠቀሱ ኢትዮጵያውያን በስም በመጥቀስ የዘረዘሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ በአሁኑ ወቅት ያለው ትውልድ ከእነዚህ ኢትዮጵያውያን በመማር አእምሯቸውን ለመልካም አስተሳሰብና ለፈጠራ ተጠቅመው የላቀች ኢትዮጵያን ለመገንባት እንዲተባባሩ ጠይቀዋል። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ገለጻ ዘረኝነትና ጥላቻ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ጥፋት መሆኑን በዘመናት መካከል ትምህርት ተወስዷል። “ጥላቻ የሚያኮስስን እንጂ የማያለመለምን በመሆኑ የተደመረ፣ የተሰናሰለ የተቀናጀ አገር ለትውልድ እንድናስተላልፍ አደራ”  ብለዋል። ዜጎች በአካባቢ ጽዳትና ችግኝ ተከላ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱም ጠይቀዋል። የኢኖሼሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው በአገሪቱ እምቅ የፈጠራ አቅም መኖሩን ገልጸው ተሸላሚዎቹም የዚህ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል። የቴክኖሎጂ ስራዎችን የሚሰሩ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎችን በማበረታታት የማህበረሰቡን ኑሮ በቴክኖሎጂ ለማገዝ ብሎም ለዓለም ገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ጉዞውን ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የፈጠራ ባለሙያዎች የቴክኖሎጂ ስራዎቻቸውን ከግብ በማድረስ ራሳቸውንና አገራቸውን የሚረዱበትን መንገድ ለማመቻቸት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ማዕከል ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም