በአማራ ክልል የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በሰላም ተጠናቀቀ

124
ሰኔ 5/2011በአማራ ክልል ላለፉት ሦስት ቀናት ሲሰጥ የቆየው የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከጥቃቅን ችግሮች በስተቀር የጎላ ችግር ሳያጋጥም በሰላም መጠናቀቁን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ። በክልሉ 285 ሺህ 334 ተማሪዎች ፈተናውን መውሰዳቸውም ታውቋል። የቢሮው የፈተናና ትምህርት ምዘና ጥናት ቡድን መሪ አቶ ማማሩ ላቀ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በቅድመ ዝግጅት ወቅት ስራዎች በመሰራታቸው በፈተና ወቅት የጎላ ችግር ሳያጋጥም ፈተናው ተጠኗቋል። ከአጋጠሙ ውስን ችግሮች መካከል የፈተናን ደንብ በመተላለፍ ለሌላ ሰው ሲፈተኑ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ስድስት ግለሰቦች በህግ ጥላ ስር እንዲውሉ መደረጉን ጠቅሰዋል። በምዕራብ ጎጃም ዞን ጅጋ የፈተና ጣቢያ አራት፣ በደቡብ ጎንደር ዞን ጋህሳይና ፈርጥ የፈተና ጣቢያዎች ሁለት ሰዎች ለሌላ ሰው ሲፈተኑ በመጀመሪያው ቀን በቁጥጥር ስር ውለዋል። በምስራቅ ጎጃም ሞጣ ከተማ አየር ማረፊያ ትምህርት ቤትና በደቡብ ወሎ ዴንሳ የፈተና ጣቢያዎች አጋጥሞ የነበረውን የመልስ መስጫ ቅጽ እጥረት ከአካባቢ የፈተና ጣቢያዎች ፈጥኖ በማምጣት ችግሩ እንዲቀረፍ መደረጉን ጠቁመዋል። በተጨማሪምፈተናው በተጀመረ በሁለተኛው ቀን በዋግህምራ ዞን ጋዝጊብላ ወረዳ ላምባ የፈተና ጣቢያና በደሴ ከተማ አስተዳደር በፈተና ወቅት ሁለት የግል ተፈታኞች መውለዳቸውን አስረድተዋል። ተማሪዎቹ የመጀመሪያውን ቀን ፈተና ያለምንም ችግር በሰላም መውሰዳቸውን የገለጹት አቶ ማማሩ ቀሪዎችን ፈተናዎች በወለዱባቸው ቦታዎች ላይ ሆነ እንዲወስዱ ተደርጓል ብለዋል። እንደ አቶ ማማሩ ገለጻ፣ ለሦስት ቀናት የተሰጠውን የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ከ294 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለመውሰድ ተመዝግበው 285 ሺህ 334 ተማሪዎች ተፈትነዋ። ፈተናው በተሰጠባቸው 490 የፈተና ጣቢያዎች የጎላ ችግር ሳያጋጥም በሰላም መጠናቀቁንም አስታውቀዋል። በነገው ዕለትም የ12ኛ ክፍል የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ለመጀመር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቅሰው በዚህም 93 ሺህ 357 ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱ አመልክተዋል። እሁድና ቅዳሜን ሳይጨምር ከነገ ሰኔ 6 እስከ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ፈተናው እንደሚሰጥም አቶ ማማሩ ጠቁመዋል። ለፈተናውም 228 የፈተና ጣቢያዎች የተዘጋጁ ሲሆን ከሦስት ሺህ የሚበልጡ ተፈታኞች፣ ተቆጣጣሪዎችና የፈተና ጣቢያ ኃላፊዎች መሰማራታቸውም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም