የአባቱን ሕይወት ለመታደግ በቀን 5 ጊዜ ለመመገብ የተገደደው የ11 ዓመቱ ታዳጊ

83
ሰኔ 5/2011 የ11 ዓመቱ ታዳጊ የአባቱን ሕይወት ለመታደግ በየቀኑ 5 ጊዜ ለመብላት ተገዷል። ነገሩ ወደ ሀገረ ቻይና ይወስደናል፤ ሉ ዚኩዋን የተሰኘው ታዳጊ በሄናን ግዛት ሺንሺያንግ ከተማ ውስጥ ከቤተሰቦቹ ጋር ይኖራል። ከሰባት ዓመታት በፊት የሉ ዚኩዋን አባት ታሞ ምርመራ ያደርጋል። በምርመራው ውጤትም የደምን ወይም የአጥንት መቅኔ (አጥንት ውስጥ ያለ የደም ህዋሶች የሚመረቱበት ለስላሳ አካልን) የሚያጠቃ በሽታ (ካንሰር) ሰለባ መሆኑ ተነግሮታል። እስካሳለፍነው ነሐሴ ወር ድረስ ህክምና ሲደረግለት ቢቆይም የአጥንት መቅኔው በጣም ቀንሶ ይገኛል። ሀኪሞችም የታማሚውን ህይወት ለመታደግ ብቸኛው አማራጭ ከቤተሰቦቹ ውስጥ መቅኔ ለግሶ ንቅለ ተከላ ማድረግ እንደሆነ ይወስናሉ። በዚህም መሠረት ለታማሚው ተቀራራቢ መቅኔ ለመስጠት ቤተሰቦቹ በሙሉ ተመርምረው የአጥንት መቅኔውን መለገስ የሚችለው በወቅቱ እድሜው 10 ዓመት የነበረው ታዳጊ ሉ ብቻ ሆኖ ተገኘ። ታዳጊ ሉ ይህንን ሲሰማ በህጻንነት አቅሙ የአባቱን ሕይወት ለመታደግ የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ቆርጦ ተነሳ። ሆኖም የልጁ ክብደት 30 ኪሎ ግራም ብቻ መሆኑ መቅኔውን መለገስ እንደማይችል በመነገሩ  ሌላ ጭንቀት ተፈጠረ። አባቱን የማዳን ብቸኛ አማራጭ ሆኖ የቀረበው ታዳጊ ሉ 45 ክሎ ግራም ክብደት ካልሞላ መቅኔ መስጠት ስለማይችል ክብደቱን ለመጨመር በየቀኑ ስብ የበዛባቸውን ምግቦች አብዝቶ ለመብላት ወሰነ። በዚህም መሰረት ካሳለፍነው መጋቢት ወር ጀምሮ በየቀኑ አምስት ጊዜ ያህል ስብ የበዛበትን ስጋ እና ሩዝ እየተመገበ ሲሆን ክብደቱም በፍጥነት እየጨመረ ነው ተብሏል።   ህጻን ሉ ”አባቴን ለማዳን ስል የሚጎዳኝን ነገርም ቢሆን ከማድረግ ወደ ኋላ አልልም፤ እኔ እና ቤተሰቦቼ አባቴን ማጣት አንፈልግም” ሲል ለቻይና መገናኛ ብዙሃን ተናግሯል። ሆኖም የሉ አመጋገብ የቤተሰቦቹን የገቢ አቅም እየፈተነው ለገንዘብ ችግር መዳረጋቸውም በዘገባው ተጠቅሷል። እናቱ ሊ ጂንጌ ተቀጥራ ከምትሰራበት ድርጅት በየወሩ 2 ሺህ ዩዋን ቢከፈላትም ቤተሰቡ የኑሮ ጫናውን መቋቋም አልቻሉም። በዚህም ምክንያት በየዕለቱ ማታ ማታ ከምትሰራበት የንግድ ተቋም ስጋ በርካሽ ዋጋ እየገዛች ልጇን ለመመገብ  ተገዳለች። የሉ የትምህርት ቤት ጓደኞች በታዳጊው የሰውነት ለውጥ ላይ ሲያዩ “ወፍራሙ ልጅ” እያሉ መሳለቅ ጀምረው ነበር። ሆኖም ሉ አባቱን ለመታደግ በየቀኑ አምስት ጊዜ ለመብላት መገደዱንና መወፈሩን ሲሰሙ እንዳስገረማቸውና ሉን በገንዘብ ለማገዝ ንቅናቄ መጀመራቸው ተሰምቷል። የሉ አድራጎት በቻይናና ሌሎች የእስያ ሀገራት መነጋገሪያ ሆኖ “ አይዞህ፣ አንተ አባትህን ለመታደግ የወሰንክ ጀግና ነህ፣ በገንዘብ እናግዝሃለን” የሚሉ አድናቆትና ችሮታዎች እየደረሱት መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል በልዩ ዘገባው ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም