የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አርሶ አደሩ የምርቱን ዋጋ እንዲወሰን አቅም ፈጥሯል

71
ሰኔ 5/2011 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሚፈጥረው የገበያ ስርዓት አርሶ አደሩ የምርቱ ዋጋ ተቀባይ ብቻ ሳይሆን የዋጋ ተማኝ እንዲሆን እያስቻለው መሆኑን ተገለጸ። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሚፈጥረው የገበያ ስርዓት አርሶአደሩ የምርቱ ዋጋ ተቀባይ ብቻ ሳይሆን የዋጋ ተማኝና ተደራዳሪ እንዲሆን እያስቻለው መሆኑም ተገለፀ። የምርት ገበያው ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ሑመራ ያሰራውን የኤሌክቶኒክስ የግብይት መስጫ ማዕከል ዛሬ አስመርቋል። ማዕከሉን የመረቁት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር እንደገለጹት የምርት ገበያው የሚያደርገው እንቅስቃሴ አገራችን ወደ ውጭ የምትልካቸው የግብርና ውጤቶች ዓይነታቸውና ብዛታቸው እያደገ እንዲመጣ እያገዘ ነው። የምርት ገበያው አርሶ አደሩ የምርቱን ዋጋ ከደላሎችና ሌሎች ነጋዴዎች ተፅእኖ ስር በማላቀቅ በራሱ ፍላጎት እንዲወስን አቅም የፈጠረለት መሆኑንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ በበኩላቸው በአገሪቱ ያለውን የገበያ ስርዓት ለማዘመን መንግስት ባለው ቁርጠኝነት መሰረት ማዕከሉ ሊገነባ መቻሉን አስረድተዋል። ማዕከሉ የከተማው መስተዳድር በነፃ በሰጠው መሬት የተገነባ ሲሆን በአንድ ጊዜ 90 አቅራቢዎች በማዕከሉ ሶፍትዌር በተገጠመላቸው ኮምፒውተሮች ታግዘው ወደ ቀጥታ ገበያው እንዲቀርቡ የሚያደርግ አቅም ያለው መሆኑንም አስረድተዋል። "ከእዚህበፊት አቅራቢዎች ምርታቸውን ለመሸጥ አዲስ አበባ ድረስ በመጓጓዝ ያካሔዱት የነበረውን የዋጋ ስምምነት በአካባቢያቸው  በኤሌክትሮኒክስ ታግዘው እንዲወስኑ ስለሚያደርግ ጊዜንና ወጪን የሚያድን አሰራር ነው" ብለዋል ። በኤሌክትሮኒክስ የመገበያየት ስርዓቱ በ2007 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተጀመረ ሲሆን እስካለፈው ግንቦት ወር ድረስ 113 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን የግብርና ምርቶች ማገበያየት መቻሉን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት የምርት ገበያው የሚጠቀምበት የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ከአዲስ አበባ ውጭ ከሀዋሳ ቀጥሎ የሑመራው ሁለተኛው ሲሆን በቅርቡም በጅማ፣ ነቀምት፣ አዳማ፣ ጎንደርና ኮምቦልቻ ለመክፈት እቅድ መያዙን ገልፀዋል። በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዓርግ የትግራይ ክልል ንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃም ተኸስተ በበኩላቸው የማዕከሉ መገንባት ጥራት ያለው ምርት በብዛት በማቅረብ የአርሶ ደሩን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል። የግብርና ምርቶች የተሻለ የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ የክልሉ መንግስት ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ዶክተር አብርሃም ተናግረዋል። አቶ ማውጫ ገብረእግዚአብሔር የተባሉት የሰሊጥ አቅራቢ ባለሃብት በበኩላቸው ከአርሶ አደሮች የሚገዙትን ምርት በአካባቢያቸው ሆነው ሌላ ተጨማሪ ወጪ ሳያወጡ ለላኪዎች ለማቅረብ የሚያስችል እድል በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል ። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚገለገልባቸውን መጋዘኖች ለመገንባት የሚያስችል የመሰረት ድንጋይ በሑመራ ከተማ ዛሬ ተቀምጧል ። የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔርና የክልሉ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃም ተከስተ ናቸው። የምርት ገበያው ለግንባታው 40 ሚሊዮን ብር እንደመደበና በቀጣዩ ዓመት የግንባታ ስራው እንደሚጀመር ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተመሰረተ 11 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን እስካሁን ድረስ 203 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አምስት ሚሊዮን ቶን የግብርና ምርቶች ማገበያየቱ ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም