ወቅቱን የሚመጥን የታክስ አሰባሰብ ስርዓት አለመዘርጋቱ ለታክስ አሰባሰብ እንቅፋት መሆኑ ተጠቆመ

82
ሰኔ 5/ 2011 በኢትዮጵያ ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢ መሰብሰብ ያልተቻለው ወቅቱን የሚመጥን የታክስ አሰባሰብ ስርዓት ባለመዘርጋቱ ነው ሲሉ “ኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ወርልድ ባንክ ግሩብ” ገለጸ። የአማራ ክልል ገቢዎች፣ የአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና የአለም ባንክ በኢትዮጵያ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በጋራ ያዘጋጁት የታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ፎረም ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል። በፎረሙ ላይ “ የንግድ ሥራ ግብይት ስርአት ችግሮች “ በሚል ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ወርልድ ባንክ ግሩፕ የታክስ አማካሪ ዶክተር ወለላ አባይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የታክስ አሰባሰብ ስርዓት ዘመናዊ አይደለም። በዚህም ሃገሪቱ ካላት ጠቅላላ የኢኮኖሚ እድገት 10 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ ታክስ እየሰበሰበች መሆኗን ጠቁመው፣ ይህም ከዓለም ሆነ ከአፍሪካ ሃገራት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንዳስቀመጣት ተናግረዋል። በታክስ በኩል ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ ያለው ከትክክለኛ ዋጋ በታች ደረሰኝ ማዘጋጀትና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ሃገር የሚገቡ እቃዎች ገበያ ውስጥ መኖር መሆኑን አስታውቀዋል። ለዚህም መንግስት ወቅቱንና የአገሪቱን ህዝብ ንቃተ ህሊና የሚመጠን የግብር አከፋፈል ስርዓት ሊዘረጋ ባለመቻሉ እንደሆነ አስረድተዋል። “ይህ ደግሞ ህጋዊ ነጋዴዎች ግብርን በቀላሉና ውጣ ውረድ ሳይበዛ እንዲከፍሉ ካለማስቻሉ በተጨማሪ ህጋዊ ያልሆኑ ነጋዴዎች እንዲበራከቱ እያደረገ ነው” ብለዋል። በመሆኑም መንግስት የግብር አሰባሰቡን ሊያዘምኑ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመዘርጋት ህጋዊ ነጋዴዎችን ከለላ መስጠትና ህገወጦችንም በቴክኖሎጂ ታግዞ መቆጣጠር የሚቻልበትን ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት አመልክተዋል። የአማራ ክልል ችግሩ በስፋት የሚስተዋልበት በመሆኑ የክልሉ መንግስት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ነው የጠቆሙት። በክልሉ ግብር የመክፈል ባህል እያደገ ቢሆንም አሁንም ብዙ ተግዳሮቶች እንዳሉ የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መንገሻ ፈንታው ናቸው። በየደረጃው ያሉ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በወቅቱ እንደከፍሉ ከማድረግ አኳያ መሻሻሎች ቢኖሩም በርካታ ህገ ወጦች መኖራቸውን ጠቁመዋል። እነዚህን አካላት ወደህጋዊነት ለማምጣት የመላው ህብረተሰብ ድርሻ የጎላ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል። በባህር ዳር ከተማ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ሙላት አስፋው በበኩላቸው “መንግስት በአሁኑ ወቅት ግብር እያስከፈለባቸው ያሉ ህጎች ከ50 ዓመታት በፊት የተዘጋጁና የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘቡ ናቸው” ብለዋል። አሁን ያለውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚመጥን አሰራርና የነጋዴውን ህብረተሰብ ንቃተ ህሌና ያገናዘበ እንዳልሆነም ተናግረዋል። ይህ ደግሞ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች እንዲበዙ ከማድረጉ በተጨማሪ ህጋዊ ነጋዴው ኋላ ቀር የአሰራር ስርአትን ተከትሎ እንዲቆይና ግብሩን በወቅቱ እንዳይከፍል እያደረገው መሆኑን አስረድተዋል። “የመንግስትን ግብርን በአግባቡ ለመሰብሰብ ካሰበ በቅድሚያ የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን ማሻሻልና ወቅቱን የሚመጥን ማድረግ ይኖርበታል” ሲሉ ገልጸዋል። መንግስት የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን ዘመናዊ ካለማድረጉ በተጨማሪ ለሥራው አቅም ያላቸውን ባለሙያዎችን እየመደበ አለመሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ጫኔ መንገሻ የተባሉ ነጋዴ ናቸው። መንግስት አሁን የንግድ አሰባሰብ ስርዓት ላይ ወደ ቅጣትና ማስገደድ ከመሮጡ በፊት ነጋዴውን ማንቃትና ለችግሮቹ የመፍትሄ አካል ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል። በፎረሙ ላይ ነጋዴዎች፣ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች፣ የክልሉ መንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ተወካዮች ተሳትፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም