ኢትዮጵያ ከ3.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ሆነች - የተመድ ሪፖርት

73
ሰኔ 5/2011 ኢትዮጵያ ባለፈው የአውሮፓ ዓመት ከ3.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ መሆኗን የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የንግድና ልማት ድርጅት አስታወቀ። የምጣኔ ኃብት ፖሊሲ ማሻሻልን ጨምሮ አስፈላጊ ሌሎች እርምጃዎች ከተወሰዱ አገሪቱ በመጪው ዓመት እስከ አምስት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ትችላለችም ተብሏል። የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የንግድና ልማት ድርጅት (አንክታድ) የ2019 የኢንቨስትመንት ሪፖርቱን ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ይፋ አድርጓል። በድርጅቱ የቀድሞ በዝቅተኛ እድገት ደረጃ የሚገኙ አገራት ልዩ ፕሪግራም ዳይሬክተር ዶክተር ታፈረ ተስፋቻው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ሆናለች። ኢትዮጵያ የተሻለ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ካስመዘገቡ አምስት የአፍሪካ አገራት መካከል መሆኗንም አስረድተዋል። ኢትዮጵያ፣ ሞሮኮ፣ ኮንጎ፣ ግብጽና ደቡብ አፍሪካ ከመላው አፍሪካ ጥሩ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የመሳብ አገራት ተብለው በሪፖርቱ መገለፃቸውም ተመልክቷል። አገሪቷ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2017 ያስመዘገበችው የውጭ ቀጥታ የኢንቨስትመንት 4.1 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን በተከታዩ 2018 ደግሞ 3.3 ቢሊዮን ዶላር አስመዝግባለች። የአለም ገበያ መዋዥቅና በአገሪቷ ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲቀንስ እንዳደረገው ጠቅሰው ይሁንና አገሪቷ አሁንም ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛና ከአፍሪካ ደግሞ ከአምስቱ አገራት አንዷ ነች ሲሉ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ከፍ ለማድረግ የቻለችው 70 በመቶ የሚሆነው ኢንቨስትመንት በማኑፋክቸሪንግ ሴክተር መዘርጋት በመቻሏ እንደሆነ ከሪፖርቱ ማወቅ ተችላል። ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም ብትጠቀም የበለጠ ውጤት ማስመስገብ እንደምትችል በሪፖርቱ መመላከቱን አክለዋል። ለዚህም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በብቃት መጠቀም፣ አዳዲስ በሚገነቡት ውስጥ ደግሞ ባለሃብቶችን በተቻለ ፍጥነት ማስገባት፣ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማካሄድ፣ የፕራይቬታይዜሽንና የፖሊሲ ማሻሻያዎች በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል ሲሉ ነው ዶክተር ታፈረ የመከሩት። ይህም እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በመጪው 2020 አገሪቷ አምስት ቢሊዮን ዶላር መሳብ ያስችላታል ሲሉ አብራርተዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየው በበኩላቸው ሪፖርቱ ገላጭ፣ጠቃሚ ሃሳቦችና ምክሮችን ያስቀመጠ ሪፖርት ነው። በቀጣይ በአገሪቷ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለመጨመር በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያየ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል። የህግ ማዕቀፎችን የማዘጋጀትና የነበሩትን የማሻሻል ተግባር እየተከናወነ እንደሆነ ተናግረው ይህም  የካፒታል፣ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ፍሰትን ለማሳደግ ያለመ ነው ሲሉ አመለክተዋል። ጠንካራና ዘመናዊ የኢንቨስትመንት አሰራር ለመዘርጋት፣ ውጤትን መሰረት ያደረገ ማበረታቻ ለማቅረብ፣ አለም አቀፍ ደረጃዎችን በሟሟላት ተወዳዳሪ ለመሆን፣ የኢንቨስትመንት ሴክተሮች ለዳያስፖራም ጭምር ተደራሽ የሚሆኑትን አሰራር ለመዘርጋት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም