በኤሌክትሮኒክስ በመታገዝ የንብረት ግዢ ለመፈጸም የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ

82
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2010 በአገሪቱ ለመንግስት ተቋማት የሚውሉ የንብረት ግዢዎች በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ የታገዙ እንዲሆኑ የሚያስችል ቅድመ ጥናት መደረጉን የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጆንሴ ገደፋ እንደገለጹት፤ በመንግስት ተቋማት የሚፈጸሙ የንብረት ግዥዎችን ቀልጣፋና ከብልሹ አሰራር የጸዱ ለማድረግ የግዢ ሂደቱን በኤሌክትሮኒክስ ስርዓት ለማከናወን እየተሰራ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከአለም ባንክ በተገኘ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ባለፉት 2 ዓመታት የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ከግምት ውስጥ ያስገባ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በአገሪቱ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) መሰረተ ልማት ያለበት ደረጃ፣ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ያለው ቅርበት፣ የኢንተርኔት አቅርቦት እና የግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ያለውን አቅም ላይ ጥናት መደረጉን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በጥናቱ ውጤት መሰረት በአገሪቱ የንብረት ግዢ  ሂደትን በኤሌክትሮኒክስ ስርዓት ለመፈጸም የሚያስችል አቅም ላይ እንደተደረሰም መረጋገጡን አቶ ጆንሴ ተናግረዋል፡፡ የሚፈጸሙ የንብረት ግዢዎችን በኤሌክትሮኒክስ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ በአሁኑ ወቅት ስትራቴጂውን እውቅና የመስጠት፣ ባለሙያና ግብዓት የማሟላት ተግባር እንደሚከናወንም ተጠቁሟል፡፡ ለሙከራ በተመረጡ ስድስት ተቋማት በሚቀጥለው አመት በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ የንብረት ግዢ ሂደት እንደሚከናወን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በ2ኛው አመት ሙሉ ለሙሉ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ መታቀዱን ጠቅሰዋል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አህመድ ቱሳ በበኩላቸው የኤሌክትሮኒክስ የንብረት ግዢ ስርዓቱ ከሰው እጅ ንክኪ የጸዳና ግልጽነትን የተላበሰ እንደሚያደርገው ተናግረዋል። የኤሌክትሮኒክስ ስርዓቱ ሲዘረጋ የንብረት ግዢ ሂደቱ የጊዜ አጠቃቀምን ከማሳጠሩም ባለፈ በዘርፉ የሚፈጸሙ የጥራትና ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረት የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም