ከመጠላለፍ በመውጣት በመተጋገዝና በመረዳዳት ለውጡን ማስቀጠል ያስፈልጋል …አቶ ደመቀ መኮንን

49
ሰኔ 5/2011 በህዝብ የጸና ትግል የመጣው ለውጥ ግቡን እንዲመታ ከመጠላለፍ በመውጣት መተጋገዝና መረዳዳት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ። በአማራ ክልል በዴሞክራሲ ምህዳር ማስፋት በሰላምና ጸጥታ ዙሪያ የሚመክር መድረክ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተጀምሯል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ ላይ እንዳሉት አሁን እየታየ ያለው ለውጥ እንዲመጣ የአማራ ክልል ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመሆን ጉልህ ድርሻውን ተወጥቷል። ለውጡ የህይወት መስዋዕትነት ጭምር የተከፈለበትና ሃገሪቱን ወደ አዲስ የፖለቲካ ምህዳር እንድትገባ ያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። በዚህም በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡ ቢሆንም ለውጡን የሚገዳደሩ ችግሮች እየተስተዋሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ለውጡ የሚመራበት የፖለቲካ የኢኮኖሚ የሰላም የዴሞክራሲና መሰል ጉዳዮች የሚቀርቡበት ማዕቀፍ ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ ለውጡ ግቡን እንዳይመታ በመጠላለፍ አለመተማመን እንዲፈጠር ሆን ተብሎ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። “በዚህ ዘመን የግል ጥረትና የቡድን ጥምረት ያስፈልጋል” ያሉት አቶ ደመቀ ወዳጅን እያበዙ ጠላትን እየቀነሱ ለውጡ ግቡን እንዲመታ በጋራ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል። በተበታተነና ባልተደራጀ አግባብ ለውጡ ፍጥነቱንና ጥልቀቱን ጠብቆ እንደማይሄድ ገልጸው በብስለትና በሰከነ አካሔድ መተጋገዝ እንደሚገባም አስረድተዋል። “ለለውጡ የሚበጀን አደናቃፊ ጉዳዮችን ወደ ጎን በመተው እንደክልልም ሆነ እንደ ሃገርም ወደ ላቀ ከፍታ ለመውጣት ህዝቡ ከአመራሩ ጎን ሆኖ ሊያግዝ ይገባል” ብለዋል። የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን በበኩላቸው “በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እየተሰራ ነው” ብለዋል። ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከለውጡ ጋር በተያያዘ በርካታ ስኬቶች ቢመዘገቡም ችግሮችም የተስተዋሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። የተገኙ ለውጦችን በማስቀጠልና ችግሮችን በመፍታት ወደ ፊት ለማራመድ ውይይቱ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል። ውይይቱ ዛሬና ነገ የሚቆይ ሲሆን በክልሉ ውስጥና ከክልሉ ውጭ የሚገኙ የአማራ ክልል ተወላጅ ምሁራን የኃይማኖት አባቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል። “ለውጡ የደረሰበት ደረጃ ፣ያጋጠሙ ችግሮችና መፍትሔዎች” በሚል ርዕስ ዛሬ የቀረበውን ጥናት ጨምሮ በሁለት ጥናታዊ ጽሁፎች ላይ ውይይት እንደሚካሔድ ከመርሀ-ግብሩ ማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም