በፖለቲካው መስክ የተመዘገበውን ስኬት በኢኮኖሚውም ለመድገም እየሰራን ነው…የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት

63
ሰኔ 4/2011 ህዝቡ የለውጥ ተጠቃሚነቱ ከፍ እንዲል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍታት ጀምሮ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚገባ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ነዋሪዎች ጠየቁ። የህዝቡን አንድነት በማጠናከር በፖለቲካው መስክ የተገኘውን ድል በምጣኔ ኃብትም በመድገም የክልሉን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል። የክልሉን የኢኮኖሚ አብዮት እንቅስቃሴ በፈተሸውና ትላንት በከተማው በተካሔደው ውይይት ላይ የተገኙት ተሳታፊ ሼህ ቃሲም ኡስማን እንዳሉት በዞኑ በኢንቨስትመንት ተይዞ ባልለማ መሬት፣ በመልካም አስተዳደርና በቴክኖሎጂ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ይሻሉ። “በኢንቨስትመንት ስም መሬት ወስደው ሳያለሙ ከልለው የተቀመጡና አስፈላጊውን የስራ እድልም ሆነ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ላይ ክፍተት የሚታይባቸውን ባለሀብቶች በማጣራት የእርምት እርምጃ ሊሰጥበት ይገባል” ብለዋል። ወጣቱን ማዕከል ያደረገ የሥራ እድል ፈጠራ አለመኖር ፣ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ አለመስጠትና የልማት ፕሮጀክቶች መዘግየት የሚስተዋሉ ጉድለቶች በመሆናቸው ሊስተካከሉ እንደሚገባ የጠቆሙት ደግሞ ከጊኒር ወረዳ የመጡት ተሳታፊ አቶ ሚሊዮን አብዲሳ ናቸው። የመዳ ወላቡ ወረዳ ተወካይ አቶ መሐመድ ሀሰን በበኩላቸው ተጀምረው ሳይጠናቀቁ ዓመታትን ያስቆጠሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ አስታውሰዋል። ህብረተሰቡ በፍጥነት ተጠናቀው አገልግሎት ይሰጡኛል በሚል በተስፋ የሚጠብቃቸው የልማት ፕሮጀክቶች በዘገዩ ቁጥር የህዝብ ቅሬታ ማስነሳታቸው እንደማይቀር ጠቁመዋል። መድረኩን የመሩት የኦሮሚያ ክልል የኢንተርፕራይዞች ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ በሰጡት ምላሽ እንደተናገሩት የህዝቡን አንድነት በማጠናከር በፖለቲካው መስክ የተገኘውን ድል በምጣኔ ኃብት ዘርፍ በመድገም የበለፀገች ኦሮሚያን ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡ ከባሌ ዞንየህዝብ ተወካዮች ጋር በኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት ላይ የተደረገው የውይይት መድረክም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በሁሉም አቅጣጫ በሚከናወኑ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው”ብለዋል። “አሁን መታየት የጀመረውን የነፃነት ብርሃን ማምጣት የተቻለው ከሁሉም በላይ የክልሉ ህዝብ አንድ በመሆኑ ነው” ያሉት አቶ ሳዳት ህዝቡ የተገኘውን ድል በመጠበቅ ኦሮሚያን በኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ሊያግዝ እንደሚገባም አሳስበዋል። ክልሉን ለማልማትም ሆነ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚቻለው ሰላምና የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑን በመረዳት ህዝቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል። የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ሀጂ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት የህዝቡን እውቀት ፣ጉልበትና ገንዘብ በማቀናጀት በጋራ ሰርቶ ከድህነት ለመውጣት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።በተለይ የክልሉ ወጣቶች የስራ አጥነት ችግር እንዲፈታ የክልሉ መንግስት ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መድቦ ወደ ስራ መገባቱንም አስረድተዋል። በተለይ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ቴክኖሎጂን መጠቀም እንዲሁም የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ማፋጠን ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አስርድተዋል።በመድረኩ ላይ ከዞኑ 18 ወረዳዎችና ሶስት የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የህዝብ ተወካዮች በኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት ዙሪያ ለመነሻ በቀረበ ፅሁፍ ላይ ተወያይተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም