በጋምቤላ ፈተና ለሌሎች ሰዎች ለመፈተን የሞከሩ ስድስት ሰዎች ተያዙ

49
ሰኔ 5/2011 በጋምቤላ ክልል የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ለሌሎች ሰዎች ለመፈተን የሞከሩ ስድስት ሰዎች መያዛቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ። በክልሉ በሁለት የፈተና ጣቢያዎች ሦስት ሴት ተፈታኞች በፈተና ላይ እያሉ ልጅ መውለዳቸውንም ቢሮው አስታውቋል። የቢሮው ኃላፊ አቶ ቶማስ የማሎ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ ትናንት በተሰጠው ፈተና ለሌላ ሰው ለመፈተን ሲሞክሩ የተያዙት በኢታንግ ልዩ ወረዳ በሚገኘው ተርቼዲ የፈተና ጣቢያ ነው። ለሌላ ለመፈተን ሲሞክሩ ከተያዙት ግለሰቦች መካከል አንዷ ሴት መሆኗን የገለጹት ኃላፊው ግለሰቦቹ በአሁኑ ወቅት በህግ ቁጥጥር ስር ውለው የፍርድ ሂደታቸውን እየተጠባበቁ መሆኑን ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ የተለያዩ የፈተና ጣቢያዎች በተደረገ ፍተሻና ክትትል 120 የሞባይል ስልኮች ወደመፈተኛ ክፍል ሊገቡና ከገቡ በኋላ መያዛቸውን ተናግረዋል። በተለይ በሞባይል የጽሁፍ መልዕክት ተልኮላቸው ፈተናውን ለመስራት ሲሞክሩ የተገኙ ተፈታኞች ሲፈተኑት የነበረው ፈተና ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ መደረጉን አስታውቀዋል። በተያያዘ ዜና በክልሉ ባለፉት ሁለት ቀናት በተሰጠው ፈተና በሁለት የፈተና ጣቢያዎች ፈተናውን እየወሰዱ የነበሩ ሦስት ተፈታኞች ልጅ መውለዳቸውን አቶ ቶማስ ገልጸዋል። ተፈታኖቹ የወለዱት “ጎርገንግ” እና “መታር” በተባሉ የፈተና ጣቢያዎች መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው በአሁኑ ወቅት ተማሪዎቹ እንክብካቤ እየተደገላቸው ቀሪ ፈተናዎችን እየወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከተጠቀሱት ችግሮች በስተቀር ፈተናው በሰላማዊ መንገድ እየተጠሰ መሆኑን ገልጸው ነገ የሚጀመረውን የ12ኛ ክፍል ፈተናንም ስኬታማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል። በጋምቤላ ክልል ከትናንት በስቲያ በተሰጠው ፈተና ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ለሌላ ሰው ለመፈተን ሲሞክሩ መያዛቸው መዘገቡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም