ብሔራዊ ፈተና በመፈተን ላይ እያለች ምጥ የጀመራት ተማሪ ወንድ ልጅ ወለደች

64
ሰኔ 5/2011 በአዲስ አበባ የ10ኛ ክፍለ ብሔራዊ ፈተና በመፈተን ላይ እያለች ምጥ የጀመራት ተማሪ መሰረት ኃይለጊዮርጊስ በሰላም ወንድ ልጅ ወለደች። ተማሪ መሰረት ኃይለጊዮርጊስ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቤተል መካነየሱስ ትምህርት ቤት የማታ ተማሪ ስትሆን ወደ ፈተና ቦታ ስትመጣ ምጥ አልጀመራትም ነበረ። በአዲስ ከተማ መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚሰጠው ፈተና ተጀምሮ ጥቂት ደቂቃዎች እንዳለፉ ተማሪ መሰረት ምጥ ይይዛትና ፈለገ መለስ ጤና ጣቢያ ተወስዳ በሰላም ተገላግላለች። በአሁን ሰዓት ተማሪዋ  የጀመረችውን ፈተና መቀጠሏን የከተማው ፈተና አስተባባሪ አቶ ፍቀዱ ፋንታዬ በተለይ ለኢዜአ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች እየተሰጠ ያለው የ10 ክፍለ ብሔራዊ ፈተና በሰላም እየተካሄደ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢ ሞባይል ስልክ ይዘው የገቡና ለሌላ ተማሪዎች ሲፈተኑ የተያዙ ተማሪዎች ተገኝተዋል። በዛሬው ዕለት በቦሌ ክፍለ ከተማ አንድ የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ የሆነ ወጣት ለሌላ ሰው ፈተና ሲፈተን ተይዟል። አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ፈታሾች ነን ብለው በመንገድ ላይ ተማሪዎችን በማስቆም የሞባይል ስልክና ገንዘብ የመቀማት ሁኔታዎችም መስተዋሉን ጠቁመዋል። ዛሬ ከሰዓት በፊት በሚጠናቀቀው የ10 ክፍል ብሔራዊ ፈተና 57 ሺህ 442 ተፈትናዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም