የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዳኞች ለሶስት ሳምንት ምንም አይነት የዳኝነት አገልግሎት አንሰጥም አሉ

93
አዲስ አበባ ሚያዝያ 24/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዳኞች ለሶስት ሳምንት ምንም አይነት የዳኝነት አገልግሎት አንደማይሰጡ አስታወቁ፡፡ የኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች ማህበር በዳኞች ላይ እየተከሰተ በመጣው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ አካሂዷል፡፡ በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች ማህበር በሴቶችና ወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ፣በከፍተኛ ሊግ፣በብሔራዊ ሊግ እና ሌሎች ማንኛውም ፌድሬሽኑ በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ጨዋታዎችን ላለመዳኘት መወሰናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከሶስት ሳምንት በኋላ ወደ እግር ኳስ ዳኝነት ለመመለስም በርከት ያሉ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በ2010 ዓ.ም በእግር ኳስ ጨዋታዎች በስፖርታዊ ጨዋነት የተጎዱ ዳኞች ካሳ እንዲከፈላቸው እና ለሚደርስባቸው ጉዳት የህይወት መድህን ኢንሹራንስ እንዲገባላቸው ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል፡፡ በክልል በሚደረጉ ውድድሮችም ለዳኞችና ታዛቢዎች የክልል ጸጥታ ሀይሎች ጥበቃ የሚያደርጉበትን መንገድ ፌድሬሽኑ እንዲፈጥርም ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም በክልል የሚካሄዱ የእግር ኳስ ውድድሮችን ለመዳኘት አውሮፕላን በሚያርፍባቸው ቦታዎች ላይ የአውሮፕላን መጓጓዣ እንዲመቻችላቸውና ሌሎች ተያያዥ ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሟሉላቸው ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም