ኢራን ዩራኒየም የማበልጸግ ስራዋን አጠናክራ ቀጥላለች

108
ሰኔ 4/2011 ኢራን ዩራኒየም የማበልጸግ ስራዋን አጠናክራ መቀጠሏን የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ሃይል ተቆጣጣሪ ተቋም ገለጸ። የተቋሙ ዋና ኃላፊ ዩኪያ አማኖ እንደተናገሩት  ኢራን የዩራኒየም ኃይል የማምረት ስራዋን አጠናክራ መቀጠሏ ተረጋግጧል። ሆኖም በ2015ቱ ስምምነት መሰረት ኢራን ዩራኒየም ለማምረት የተጣለባት መጠነ-ገደብ ላይ የምትደርስበት ጊዜ በግልፅ እንደማይታወቅ ተናግረዋል። ቴህራን የኒዩክሌር ኃይል ማበልጸግ ስራዋን እንድታቆም እና ማዕቀቦች እንዲነሱላት በፈረንጆቹ 2015 ከዓለም ኃያላን ሀገራት ጋር ስምምነት ተፈራርማ ነበር። ባሳለፍነው ወር በመሪዋ በኩል በሰጠችው መግለጫ ከ2015ቱ ስምምነት ገቢራዊነት በከፊል ራሷን ማግለሏን ለዓለም ይፋ አድርጋለች። የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ተቆጣጣሪ ተቋም ዋና ኃላፊ አማኖ የኢራን ወቅታዊ የኒዩክሌር እንቅስቃሴ እንዳስጨነቃቸው ገልጸው፤ጉዳዩን ወደ ውይይት ማምጣት እንድሚገባ መክረዋል። የኢራን የወጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሃመድ ጃቫድ ዛሪፍ በበኩላቸው፤  አሁን የተፈጠረው ውጥረት የሚረግበው፥ በአሜሪካ የተቃጣው ኢኮኖሚያዊ ጦርነት ሲቆም መሆኑን ገልጸዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም