የአፍሪካ አገሮች የኢንተርኔት አገልገሎት በቅናሽ ዋጋ እንዲያቀርቡ ተጠየቀ

64
ሰኔ 3/2011 የአፍሪካ አገሮች ዜጎች የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማስቻል ባለፈ አገልገሎቱን በቅናሽ ዋጋ እንዲያቀርቡ ተጠየቀ። የአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። የተባበሩት መንግሥታቱ ድርጅት (ተመድ) የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሃፊ ቬራ ሶንጉዌ በተወካያቸው ባስተላለፉት መልዕክት በአፍሪካ የቴሌኮም ኢንዱስትሪው እድገት አሳይቷል። በተለይም ደቡብና በሰሜን አፍሪካ አካባቢ የቴሌኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ እድገቱ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ በሌሎችም አካባቢ መጠነኛ እድገት መመዝገቡን ገልጸዋል። ያም ሆኖ አሁንም በርካታ ሰዎች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ገልጸው ለዚህም ደግሞ በአህጉሪቱ በርካታ ውስንነቶች መኖራቸውን ተናግረዋል። እንዲያም ሆኖ መንግሥታት ለአህጉሩ እድገት ወሳኝ የሆነውን የቴሌኮም ቴክኖሎጂን ተደራሽ ለማድረግ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በተለይም ደግሞ የተቋማትን አሰራር በማዘመን፣ የንግድ ሥርዓትን በማቀላጠፍ፣ የአገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ከፍተኛ አስተዋዕዖ ያለው በመሆኑ የአገልግሎት ዋጋው ዝቅተኛ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። ይህም ዜጎች የማኅበራዊ አገልግሎግት በቀላሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ነው ያሉት። የኢኖቬሽንና የቴክኖሊጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል አቅም መኖሩን ተናግረዋል። በተለይም ባለፉት ዓመታት በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በሳይንስ ዘርፍ ተመርቀው መውጣታቸው እንደ አንድ መሰረት አንስተውታል። በአሁኑ ወቅት መንግሥት የቴሌኮም ዘርፉን ለግል ባለሃብት ክፍት ማድረጉንና በኢንተርኔት የታገዘ የክፍያና የንግድ እያንሰራራ መሆኑን ነው የጠቆሙት። በአፍሪካ የኢንተርኔት ተጠቃሚነት ምጣኔ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2005 ከነበረው 2 ነጥብ 1 አሁን ላይ 24 ነጥብ 4 በመቶ በላይ መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም