በኢትዮጵያ ለህትመት የበቁ የምርምር ውጤቶች ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ ነው

52
ሰኔ 3/2011 በኢትዮጵያ ለህትመት የበቁ የምርምር ውጤቶች ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ መሆናቸውን በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁር ገለጹ። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀው የምርምር ህትመቶች ፣ የምርምር ስነ ምግባርና የምርምር ጆርናሎች ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት አውደ ጥናት ዛሬ ተከፍቷል። በአውደ ጥናቱም በአገር አቀፍ ደረጃ የተሰሩና ለህትመት የበቁ የምርምር ስራዎች ላይ ያተኮረ ጥናት ያደረጉት በአክሱም ዩኒቨርስቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኪሮስ ጉእሽ እንደሚገለጹት በአገሪቷ የሚሰሩት የምርምር ስራዎች ብዛት ቢኖራቸውም ለህትመት የሚበቁት የምርምር ውጤቶች ቁጥር ዝቅተኛ ነው። ለአብነትም ወደ 50 የሚጠጉ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና በርካታ የምርምር ተቋማት እንዲሁም ወደ 33 ሺህ የሚሆኑ የዩኒቨርሰቲ መምህራን ቢኖሩም የሚታተሙት የምርምር ስራዎች ቁጥር ግን በጣም አነስተኛ እንደሆኑ ነው የሚናገሩት። በአጠቃላይ በአገሪቷ እስካሁን የታተሙ ምርምር ውጤቶች ቁጥር 26 ሺህ ሲሆን ይህም ከአፍሪካ 4 በመቶና ከዓለም አቀፍ ደረም ዜሮ ነጥብ 04 በመቶ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል። ለህትመት ከበቁት የምርምር ውጤቶች የአብዛኞቹ ደረጃም ዝቅ ያለና ጥራታቸው በሚጠበቀው ልክ ሳይሆን ገንዘብ በመከፈሉ ብቻ የታተሙ መሆናቸውንም ዶክተር ኪሮስ ገልጸዋል። 60 በመቶ የሚሆኑት የምርምር ውጤቶች ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር የተሰሩ መሆናቸውን የጠቀሱት ተመራማሪው፤ ይህንን  በራስ አቅምና በባለሙያ በመስራት ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ፕሮፌሰሮች ተሰርተው የታተሙ የምርምር ስራዎች ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑንም ገልጸዋል። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መምህራን በየሁለት ዓመቱ ምርምር ሰርተው እንዲያሳትሙ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም እስከ 10 ዓመት ድረስም ለህትመት የደረሰ ምርምር ያላከናወኑ መምህራን መኖራቸውን በጥናታቸው አመልክተዋል። በምርምር ስራዎች ላይ የተመሰረተ የመምህራን ዕድገትና ጥቅማ ጥቅም በአገር አቀፍ ደረጃ  ወጥ አለመሆኑ እንደምክንያት የሚጠቀስ ሲሆን፤ በዚህም ከፍተኛ የበጀት ብክነትና ሌሎች ክፍተቶች በምርምር ስራዎች ላይ መኖራቸውንም ዶክተር ኪሮስ ጠቁመዋል። በሁሉም ተቋማት የሚሰሩ ምርምሮች በተመሳሳይ ዘርፎች ላይ እንደሚበዛ በጥናት መረጋገጡን ገልጸው ተቋማት በውስንና በተመረጡ ዘርፎች ላይ እንዲሰሩ ቢደረግ የተሻለ ውጤታማ ይሆናሉ ብለዋል። ለአብነትም በኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቦች፣ በነፋስ እና በፀሀይ ብርሃንአማራጭ የኃይል ምንጮች ላይ የተሰሩ ምርምሮች ዝቅተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። በቡና፣በሰሊጥ፣ በበለስ፣ በገብስ፣ በማሽላ፣ በጤፍና በሌሎች የግብርና ምርቶች ላይም ተሰርተው ለህትመት የበቁ በቂ የምርምር ስራዎች እንደሌሉ አብራርተዋል። እንደ ዶክተር ኪሮስ ገለጻ በእነዚህ ዘርፎች ላይ በስፋት በመስራት ለአገሪቷ ዕድገት ጉልህ አስተዋዕኦ ማድረግ ይቻላል። የምርምር ስራዎች ህትመት ጥራትን ለማሳደግና ዓለም አቀፍ ደረጃን ለማስጠበቅ ብሔራዊ የህትመት ፖሊሲ ሊኖር እንደሚገባም በጥናታቸው ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም