የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በመንግስት ተወርሰው የቆዩ ህንጻዎቿን ተረከበች

71
ሰኔ 3/2011 በዋጅ 47/67 የተወረሱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ባለ 12 ወለልና ሁለት መካከለኛ ሕንፃዎች ከ24 ዓመታት ክርክር በኋላ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር ሰጪነት እንዲመለሱ መወሰኑን ተከትሎ ርክክብ ተከናውኗል። የርክክብ ሰነዱን ለአባ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ያስረከቡት የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል እንደገለጹት፤ ላለፉት ሁለት ወራት ገደማ የርክክቡ ጊዜ ሳይከናወን የዘገየው በቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ምክንያት ነው። በመሆኑም ከጠቅላይ ፓትርያርክ ጽህፈት ቤትና ከቤቶች ኮርፖሬሽን እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ጽህፈት ቤት በተወከሉ ባለሙያዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራው ሲከናወን ቆይቶ በመጠናቀቁ የማስረከቢያ ሰነዱን ዛሬ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል። ኮርፖሬሽኑ ከ1987 እስከ 1989 በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ 13 የሚሆኑ የቤተ ክርስቲያኗን ሕንፃዎች መመለሱን አስታውሰዋል። ዛሬ ርክክባቸው የተፈጸሙት እነዚህም ሕንፃዎች ላለፉት 24 ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሳይተላለፉ መቆየታቸውን የገለጹት አቶ ረሻድ፤ የቤተክርስቲያኗ ህንጻዎች ሳይመለሱ የቆዩበት ምክንያት ተመርምሮ የውሳኔ ሃሳብ እንዲቀርብ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ተገቢው ምርመራ ተካሂዶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ቀርቦ እንዲመለስ ውሳኔ እንደተሰጠበት ተናግረዋል።በመሆኑም ቤተ ክርስቲያኒቷ የተረከበችው ቤት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን አዲስ በሚሠሩ ቤቶች ውስጥ እስኪዘዋወሩ ድረሰ ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትይዛቸው አሳስበዋል። ሰነዱን የተረከቡት ብፁ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው፤ ''ለሁሉ ጊዜ አለው እንደሚለው ቅዱስ መጽሐፍ ለ24 ዓመታት እልህ አስጨራሽ ክርክር ያደረግንባቸው ቤታችንን እንዲመለስ ለፈቀደው ልዑል እግዚአብሔርና እንዲመለስልን ቁርጠኛ ትእዛዝ ለሰጡልን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ምስጋና እናቀርባለን'' ብለዋል። የርክክብ ሂደቱን ከቤተ ክርስቲያኒቱ በመወከል ሲያስፈጽም የነበረው ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት እንዳመለከተው፤ ተወርሰው የነበሩ ሁለት ባለ 12 ወለልና ሁለት አነስተኛ ሕንፃዎችን መረከቡን ጠቁመው፤ ነገር ግን በተመለሱት ሕንፃዎች ይዞታ ላይ የሚገኙና የቤቶች ኮርፖሬሽን የማያስተዳድራቸው ሕንፃዎች መኖራቸውን አስረድቷል። በመሆኑም የፓትርያርክ ጽህፈት ቤት ያልተረከባቸውን ቤቶች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንዲያስመልሳቸው እንዲደረግ ኮሚቴው አስተያየቱን አቅርቧል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም