መንግስት ሕጻን አበጥር ወርቁን በውጭ አገር ለማሳከም ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለፀ

90
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2010 ሕጻን ብርሃኑ (አበጥር) ወርቁ በውጭ አገር ሕክምና እንዲከታተል መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ። አቶ ደመቀ ከተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሰቃቂ ግፍ የተፈጸመበትንና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ህክምና እየተከታተለ የሚገኘውን ህፃን አበጥርን ጎብኝተዋል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከህፃኑ ቤተሰቦችና ሕክምናውን ከሚከታተለው የሃኪሞች ቡድን ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ የህክምና ቡድኑም ህፃን አበጥር የደረሰበት ጥቃት ውስብስብ በመሆኑ ወደ ውጭ አገር ሄዶ የሚታከምበት ሁኔታ እንዲፋጠን ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩም የሕክምና ቡድኑን ጥያቄ ተቀብለው፤ በአጭር ጊዜ የውጭ አገር ህክምና እንዲመቻችለት መንግሥት የተሟላ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። የህጻኑ ጤንነት በዘላቂነት መሻሻል እንዲያሳይ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ለህጻኑ ቤተሰቦች ገልጸዋል። መንግሥት ለህፃን አበጥር ቤተሰቦች በገንዘብ የሚታገዙበትን መንገድ እንዳመቻቸና የውጭ አገር ህክምና ሙሉ ወጪው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደሚሸፈን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በህፃን አበጥር ላይ የተፈፀመው ጥቃት እጅግ አሳዛኝ እና ሰብዓዊነት የጎደለው ነው ያሉት አቶ ደመቀ ድርጊቱን የፈጸሙት ግለሰቦች በሕግ ጥላ ሥር ይገኛሉ ብለዋል። ተጠርጣሪዎች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕግ ጥላ ሥር ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነና በሕግ ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጠል አስታውቀዋል። አቶ ደመቀ ህፃን አበጥር ከደረሰበትን አስከፊ ጥቃት አንፃራዊ መሻሻል እንዲያሳይ የህክምና ድጋፍ ላደረጉ ለፈለገ-ህይወትና ለቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎችም ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም