ቼክ በሐረሪ ክልል በኢንቨስትመንት፣ በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ለመሥራት ዝግጁ ናት-አምባሳደር ሚኬሽ

71
ሐረር ሰኔ 3 / 2011  ቼክ ሪፐብሊክ በሐረሪ ክልል መግሥት ጋር በኢንቨስትመንት፣ በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን የአገሪቱ አምባሳደር ገለጹ። አምባሳደር ፓቫል ሚኬሽ ከሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወሒብ በድሪ ጋር ዛሬ ተነጋግረዋል። በወቅቱም አምባሳደር ሚኬሽ እንደተናገሩት አገራቸው  ከክልሉ መንግሥት ጋር በዘርፎቹ ለመሥራት ዝግጁ ናት። በዚህም በኢንቨስትመንት መስክ የቼክ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ ሙአለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል። አገራቸው በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ረገድ የእውቀት ሽግግርና ልምድ ለማጎልበትም ድጋፍ እንደምታደርግ  አስታውቀዋል። በተጨማሪም የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማሳደግ እንደሚሰራም  አምባሳደር ሚኬሽ አመልክተዋል። ቼክ ከቅርስና ቱሪዝም ጋር ተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ ቅርሶች ባለቤት እንደመሆኗ ልምዷን ለክልሉ በማካፈል ተጠቃሚ እንደምታደርገው ተስፋቸው የገለጹት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወሒብ በድሪ ናቸው። አምባሳደር ሚኬሽ የክልሉ መንግሥት የቅርስ ጥበቃ፣እንክብካቤና አያያዝን ለማሻሻል በሚያከናውነው እንቅስቃሴ  ለባለሙያዎች ትምህርትና ስልጠና እንዲሁም  የኢንቨስትመንትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል። አምባሳደር  ሚኬሽ በሐረር ከተማ የሚገኙ ሃይማኖታዊ፣ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦችን ጎብኝተዋል። በሸዋል ኢድ በዓል ላይ ይገኛሉም ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም