ዩኒየኑ ከዕጣንና ሙጫ ምርት 10 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለፀ

94
ሰኔ 3/2011 በምዕራብ ጎንደር ዞን የተፈጥሮ ሀብትን በመንከባከብ እጣንና ሙጫ አምርቶ ለገበያ ያቀረበ ዩኒየን ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገለፀ ፡፡ ቴውድሮስ የተፈጥሮ አብት የዩኒዬን ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳለ ጌታ ለኢዜአ እንደገለፁት ገቢው የተገኘው ከ27 የዩኒየኑ አባል የሕብረት ስራ ማህበራት 1 ሺህ ኩንታል የእጣን ምርት ሰብስቦ ለገበያ በማቅረብ ነው ። ዩኒየኑ ለገበያ ለማቅረብ ያዘጋጀውና 5 ሚሊዮን ብር ዋጋ የሚያወጣ ተጨማሪ 500 ኩንታል የዕጣንና ሙጫ ምርት እንዳለውም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል። የእጣንና ሙጫ ምርቱ የተሰበሰበው ለሕብረት ሥራ ማህበራት ተከልሎ ከተሰጣቸው 90 ሺህ ሄክታር የደን ሃብት ውስጥ ነው ተብሏል ። እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ዩኒዮኑ የተፈጥሮ ሀብቱን ከህገ ወጥ የደን ምንጠራ፣ ከእርሻ ስራና መሰል አደጋዎች በመከላከልና ጥንቃቄ የተሞላበት የምርት ስርዓት በመከተል ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያስመዘገበ ነው። በመተማ ወረዳ የሻሽጌ ቀበሌ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ማህበር ሰብሳቢ አቶ ባዘዘው አላቸው በሰጡት አስተያየት 56 አባላት ያሉት ማህበራቸው ዘንድሮ 100 ኩንታል ዕጣንና ሙጫ አምርቶ ለማህበሩ በማስረከብ 1 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስረድተዋል ። የዩኒየኑ መመስረት ከእዚህ በፊት 5 ሺህ ብር ብቻ ያወጣ የነበረው የአንድ ኩንታል ዕጣን ዋጋ በእጥፍ አድጎ 10 ሺህ ብር መድረሱንና በእዚህም ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል ። ‹‹በተፈጥሮ ሀብት ልማት ተደራጅተን እጣንና ሙጫ ማምረት ከጀመርን ወዲህ የተሻለ ገቢ ማግኘት ችለናል።›› ያሉት ደግሞ በቋራ ወረዳ አዲስ ልደት ቀበሌ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ማህበር ሰብሳቢ አቶ አያና አትርሳው ናቸው፡፡ ማህበራቸው 42 አባላት ያሉት ሲሆን በዚህ ዓመት 96 ኩንታል ዕጣን አምርተው ለዩኒየኑ በማስረከባቸው ከ960 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ገልፀዋል። ዩኒየኑ 6 ሺህ አባላት ያሉት ሲሆን ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ14 ሺህ ኩንታል በላይ የእጣንና ሙጫ ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ ለአባላቱ ማከፋፈሉን ተናግሯል ። በዞኑ የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክን ሳይጨምር በመተማና ቋራ ወረዳ ብቻ ከ257 ሺህ ሄክታር በላይ የደን ሽፋን አለ ተብሏል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም