ውሳኔው ለዘላቂ ሰላም መጠበቅና ለምጣኔ ሃብት መዋቅራዊ ሽግግርና ወሳኝ ነው

108
ድሬዳዋ ሰኔ 1/2010 የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያስተላለፈው ውሳኔ ለኢትዮጵያና ኤርትራ ወንድማማች ሕዝቦች ዘላቂ ሰላምና ዕድገት መፍትሄ እንደሚያመጣ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ሙሁራን ተናገሩ። ኮሚቴው በመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች የአክሲዮን ድርሻ እንዲኖራቸው መወሰኑ የሀገሪቱን የምጣኔ ሃብት መሰረት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት እንደሚያፋጥነውም የዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሃብት መምህርና ተንታኝ ገልፀዋል፡፡ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት መምህር የሱነህ አወቀ ለኢዜአ እንደተናገሩት "አገሪቱ የምትፈልገው የዕድገት ደረጃና የህዝቦቿ ብልፅግና እንዲመጣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት ሰላማዊና የተረጋጋ መሆን" አለበት፡፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከኤርትራ ጋር ለዓመታት የነበረውን የሻከረ ግንኙነት ለማርገብና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የአልጀርሱን ስምምነት ለመቀበል መወሰኑ ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ሰላምና ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል። ሰላም ከሌለ የሀገር በጀት ለጦርነት የሚውል በመሆኑ ለዜጎች መሰረታዊ የልማትና የአገልግሎት ጥያቄዎች መፍትሄ ለመስጠት እንደሚያስቸግርኝም የህግ ሙሁሩ አቶ የሱነህ የውሳኔውን ትክክለኛነት አስረድተዋል፡፡ "በመሆኑም ዘላቂ ሰላምን ለሚያመጣው ለዚህ ጥሪ የኤርትራ መንግስት ተመሳሳይ ፍላጎት ሊያሳ ይችላል፤ ይህ አጋጣሚ ከሁለት አገሮች አልፎ ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች ጭምር ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ለማምጣት ዋስትና ይሆናል" ብለዋል፡፡ ሌላው የዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር አቶ አለምሰገድ ደጀኔ በበኩላቸው ውሳኔው ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የነበረውን ችግር የሚፈታና ለሁለቱ ሀገሮች ወንድማማች ህዝቦች ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "ከህግ አንጻር የአልጀርሱ ስምምነት ይግባኝ የሌለው አለም አቀፍ ህግ ነው፤ ህጉን የፈረምን በመሆኑ መቀበልና ማክበር ከሀገራችን የሚጠበቅ ትክክለኛ ውሳኔ ነው" ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ዜና የህግ መምህሩ አቶ አለምሰገድ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመንግስት የልማት ድርጅቶችና በሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የግል ባለሀብቱ በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ የአክሲዮን ድርሻ እንዲኖረው መወሰኑ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል። "በአለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ ስምና ዝና ካላቸው የውጭ ባለሃብቶችና ኩባንያዎች ጋር አገሪቱ ያላትን ግንኙነት የሚያጠናክርና በሀገሪቱ የተጀመረውን ዕድገት በተሻለ ለማስቀጠል መደላደል" ይፈጥራል ብለዋል፡፡ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ትምህርት ክፍል መምህርና የዘርፉ ተንታኝ አቶ ገብረክርስቶስ ገብረስላሴ ውሳኔው የዘርፉ ባለሙያዎች ሲጠብቁት የነበረ ትልቅ ውሳኔ መሆኑንና በኢኮኖሚው ውስጥ መዋቅራዊ ለውጥ እንደሚመጣ የሚያግዝ መሆኑን ተናገረዋል፡፡ የግሉ ባለሃብት በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂ የተሻለ ስለሚሆን ለውጭ ገበያ መቅረብ የሚችሉ ምርቶችን ጭምር በማምረት የሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር እንዲሸጋገር ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡ የልማት ድርጅቶች በከፊል ለግል ባለሀብቱ እንዲሸጥ መደረጉ የውጭ ምንዛሬ ችግርን ለመፍታትና ለዜጎች የሥራ ዕድል በስፋት ለመፍጠር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የገለጹት አቶ ገብረክርስቶስ የኤኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃው ከመንግስት ሸክም እንደሚያቃልል ገልጸዋል። "በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያስገኝ በመሆኑም መንግስት የተመረጡ የህዝብ፤ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በፍጥነትና በሚፈልገው ደረጃ ለመፍታት ያስችለዋል" ብለዋል፡፡ የምጣኔ ሃብት ተንታኙ እንደተናገሩት የግል ባለሃብቱ ዋና ትኩረቱ ገበያና ትርፍ በመሆኑ ድሀው ሕብረተሰብ እንደ ቴሌና የኤሌክተሪክ ኃይል ያሉ አገልግሎቶች እንዳይጓደሉበት አተገባበሩ ላይ ተገቢ ጥንቃቄ እንዲደረግ አመልክተዋል። የአገር ውስጥ ባለሀብት ከውጪ በሚመጡ ግዙፍ ኩባንያዎች እንዳይቀጭጩና እንዳይዋጡ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባም ስጋታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም