የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ያለምንም ችግር እየተካሄደ ነው

125
ሰኔ 3/2011 በአዲስ አበባ ከተማ የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ያለምንም ችግር እየተካሄደ መሆኑን የፈተና ጣቢያ አስተባባሪዎች ተናገሩ። ዘንድሮ በአዲስ አበባ 57 ሺህ 445 የመደበኛ፣ የማታና የግል ተፈታኝ ተማሪዎች የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ይወስዳሉ። በተለያዩ የፈተና ጣቢያዎች ኢዜአ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው አስተባባሪዎች እንዳሉት ፈተናው እስካሁን ያለምንም ችግር እየተካሄደ ነው። የዳግማዊ ሚኒሊክ ፈተና ጣቢያ ኃላፊ መምህር መሰረት አስፋው እንዳሉት በፈተና ጣቢያው 442 ተማሪዎች ፈተና በመውሰድ ላይ ናቸው። በፈተና ጣቢያው እየተፈተኑ ያሉት ተማሪዎች በመደበኛ፣ በማታ፣ በግል ፈተናውን የሚወስዱ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ተማሪዎች በፈተና ወቅት ማድረግ ስለሚገባቸው ባለፈው አርብ ገለፃ ስለተደረገላቸው የፈተና ስነምግባርን ተከትለው ፈተናውን እየወሰዱ ይገኛለም ነው ያሉት። የተወሰኑ ተማሪዎች አርፍደው የመጡ ቢሆንም ከፀጥታና ከፈተና አሰጣጥ ጋር የገጠመ ችግር አለመኖሩንም ኃላፊው ተናግረዋል። በፈተና ጣቢያው 929 ተማሪዎች ፈተና እየወሰዱ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የቤተልሄም ፈተና ጣቢያ የፈተና ክፍል ኃላፊ መምህርት ሀና ፀጋዬ ናቸው። ባለፈው አርብ እለት ለተማሪዎች በቂ ኦሬንቴሽን (ማብራሪያ) በመሰጠቱ እስካሁን ምንም አይነት ብዥታ ሳይኖር ያለምንም ችግር እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል። ተፈታኝ ተማሪዎች በበኩላቸው በተሰጣቸው ገለፃ ተመስርተው ፈተናውን በአግባቡ እየተፈተኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። ለዓመታት የለፉበትን የትምህርት ፍሬ ለማግኘት በቀጣዮቹም ቀናትም በተረጋጋና የተነገራቸውን ስነ-ምግባር ተከትለው እንደሚወስዱ ያነጋገርናቸው ተማሪዎች አረጋግጠዋል። ኀብረተሰቡም በተለይ ጠዋት ላይ ተፈታኞቹ የትራንስፖርት ችግር እንዳይገጥማቸው ቅድሚያ በመስጠት እንዲተባበራቸው ኃላፊዎቹ ጠይቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም