በባሌ ዞን ሀገር አቀፍ የአስረኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በተሟላ መልኩ መሰጠት ተጀመረ

63
ሰኔ 3/2011ሀገር አቀፍ የአስረኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በተሟላ መልኩ መሰጠት መጀመሩን የባሌ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ግዛው በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው የአስረኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በዞኑ 20 ወረዳዎች ውስጥ ዛሬ በተሟላ መልኩ ያለምንም የፀጥታ ችግር መሰጠት ተጀምሯል፡፡ በ57 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ዛሬ የተጀመረውን የአስረኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከ15ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች በሰላማዊ መልኩ እየተፈተኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ኃላፊው እንዳሉት ለፈተናው የሚያስፈልጉ ሁሉም ግብዓቶች በተሟላ መልኩ ቀድመው በየፈተና ጣቢያዎቹ በመድረሳቸው ፈተናውን ያለምንም ችግር እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በጎባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተፈታኝ ተማሪዎች በበኩላቸው ለፈተናው በጥራት ቡድን በመደራጀት ያደረጉት ዝግጅት በራሳቸው እንዲተማመኑና ፈተናውን በተረጋጋ መንፈስ እንዲወስዱ ያስቻለቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከተፈታኞቹ መካከል ተማሪ አቤል መስፍን ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ ከሌሎች ጓደኞቿ ጋር በጥራት ቡድን ተደራጅተው በማጥናት ለፈተናው ቀድመው ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጿል፡፡ ተማሪው እንዳለው ለፈተናው አስቀድሞ ዝግጅት ማድረጉ እውቀቱን ከማደበር በተጓዳኝ በራስ የመተማመን ብቃቱን አሳድጎለታል፡፡ በባሌ ዞን ዘንድሮ የሚሰጠውን ክልላዊና ሀገር አቀፍ ፈተና ከ38 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች እንደሚወስዱ ከዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም