በወላይታ ዞን በደረሰ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

63
ሰኔ 2/2011 በወላይታ ዞን አበላ ፋራቾ ቀበሌ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ በእርሻ ማሳና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ፤ በዞኑ ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ በደረሰ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ደግሞ የስድስት ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ የአባላ አባያ ወረዳ ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተገኝ ተፈራ እንደገለጹት ትናንት ንጋት 11፡00 ጀምሮ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የተከሰተው ጎርፍ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት አስከትሏል። "ጎርፉ በአካባቢው የሚገኙ ሀማሳ እና ዜግሬ ወንዞች በሚገናኙበት ቦታ ላይ ውሃው ሞልቶ ከወንዙ በመውጣቱ አደጋው ሊከሰት ችሏል" ብለዋል። የጎርፍ አደጋው በተለይ አበላ ፋራቾ በተባለ ቀበሌ ውስጥ በሚገኙ ላልአና እና ፋራቾ መንደሮች በእርሻ ማሳና በነዋሪዎች መኖሪያ ቤት ድረስ ዘልቆ በመግባት በቤት ንብረት፣ በቁሳቁስና በተቀመጠ እህል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡ የዝናቡ መጠን ከፍተኛ መሆኑ ወንዞቹ በሚገናኙበት ቦታ ውሃው ሞልቶ ከወንዝ በመውጣት በአርሶ አደሩ ማሳ የተለያዩ ሰብሎች ላይ ጉዳት ማስከተሉንም ተናግረዋል፡፡ በጎርፉም ከ80 በሚበልጡ አርሶ አደሮች በተለያዩ ሰብሎች ያለሙት ከ100 በላይ ሄክታር መሬት ላይ ጉዳት መድረሱን ነው አቶ ተገኝ የገለጹት፡፡ ጎርፉ በንብረትና በእርሻ መሬት ላይ ካደረሰው ጉዳት ባለፈ በሰውና በእንስሳት ሕይወት ላይ ያስከተለው ምንም ጉዳት አለመኖሩን አቶ ተገኝ ገልጸዋል፡፡ በጎርፉ ጉዳት የደረሰባቸውን ነዋሪዎች በጊዜያዊነት ለማቋቋምና የጎርፍ መከላከያ ስራን አስመልክቶ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ "የዝናቡ ሁኔታ በቀጣይ እየጨመረ ስለሚሄድ መሰል ችግሮችን ለመከላከል ህብረተሰቡ በማሳ አካባቢ የጎርፍ መሄጃ ትቦ በማዘጋጀት ቅድመ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል" ብለዋል። በጎርፉ ጉዳት ከደረሰባቸው ነዋሪዎች መካከል በፋራቾ መንደር የሚኖሩት አርሶ አደር አለማየሁ ቢቢሶ በደረሰዉ ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ቤትና በንብረታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን  ተናግረዋል። ለምርጥ ዘርና ለሌሎች ግብአቶች ወጪ በማውጣት በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ የዘሩት የበቆሎ ሰብል በጎርፉ ምክንያት ተጠርጎ መወሰዱን  ገልጸው መንግስት ፈጣን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሌላኛው የላልአና መንደር ነዋሪ አቶ አስራት ግቦሬ በበኩላቸው ከትናንት ንጋት 11፡00 ጀምሮ የተከሰተዉ ጎርፍ ቤታቸውን ሞልቶ በንብረት ላይ ጉዳት በማድረሱ ልጆቻቸውንና እንስሳትን ይዘው አስፋልት ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል፡፡ በቤት ውስጥ የነበሩ እህሎችና የቤት ውስጥ እቃዎች ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን የገለጹት ነዋሪው የተለያዩ ግብአቶችን ተጠቅመው በ2 ጥማድ ማሳ ላይ የተከሉት በርበሬ እና በሌላ 2 ጥማድ ማሳ የዘሩት ቦቆሎ በጎርፉ መወሰዱን ተናግረዋል። እንደ አርሶ አደሩ ገለጻ ከጊዜያዊ ድጋፍ ባሻገር ዳግም የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት መንግስት ለዘላቂ መፍትሄ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። በሌላ ዜና በወላይታ ዞን ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ በደረሰ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ በአንድ ታዳጊ ህጻን ላይ  ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የወረዳው ፖሊስ አስታውቋል፡፡ የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ዳዊት ዳና እንዳሉት በወረዳው ዮካሬ በሚባል የገጠር ቀበሌ ትናንት አደጋው የደረሰው በግምት ከቀኑ 4፡00 ሰዓት አካባቢ ነው። ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች በሸክላ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነዋሪዎች ሲሆኑ አደጋው የደረሰውም ለስራቸው የሚሆን አፈር ለማውጣት በቁፋሮ ላይ ሳሉ ነበር። በአደጋው በአፈር የተሸፈኑ ስድስት ሰዎች ታፍነው ወዲያው ሲሞቱ መጠነኛ አፈር ያረፈበት አንድ የ14 ዓመት ታዳጊ ህፃን ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ኢኒስፔክተር ዳዊት አስታውቀዋል። "የሟቾች አስከሬን ከተመረመረ በኋላ ለቤተሰቦቻቸው ተሰጥቷል”ብለዋል፡፡ ጉዳት የደረሰበት ታዳጊ ህጻንም በዱቦ ቅድስት ማሪያም ሆስፒታል ህክምናውን በመከታተል ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከፍተኛ ዝናብን ተክትሎ እንደዚህ ዓይነት ያልታሰቡ አደጋዎች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ነዋሪዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም ኢንስፔክተር ዳዊት አሳስበዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም