ሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎችን አስመረቀ

83
ሰኔ 2/2011 ሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በገጠርና በከተማ ጤና ኤክስቴንሽን መርሀ ግብር ያሰለጠናቸውን 311 ተማሪዎች አስመረቀ። የኮሌጁ ዲን አቶ መለሰ ዘውገ በምረቃው ላይ እንደተናገሩት ኮሌጁ በመደበኛ መርሀ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያሰለጥን ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት በክሊኒካል ነርሲንግ፣ በሚድዋይፈሪ፣ በሕክምና ላቦራቶሪ፣ በጤና መረጃ ፣ በገጠርና በከተማ ኤክስቴንሽን መርሀ ግብር እንዲሁም በድንገተኛ ሕክምናና በፋርማሲ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑን አመልክተዋል። ሰልጣኝ ተማሪዎቹ በእውቀትና በክህሎት ሙያዊ ብቃት እንዲኖራቸው እንዲሁም በስነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ ኮሌጁ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ለእዚህም ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር ልምምድ የታገዘ እንዲሆን ለማድረግ በሰርቶ ማሳያና በተለያዩ የጤና ድርጅቶች ተግባራዊ ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉን አመልክተዋል። ለምረቃ የበቁት በገጠርና በከተማ ጤና ኤክስቴንሽን መርሀ ግብር የሰለጠኑ 311 ተማሪዎች መሆናቸውን የገለጹት አቶ መለሰ፣ ተመራቂዎች በቀጣይ ወደሥራ ዓለም ሲገቡ ህብረተሰቡን በቅንነት በማገልግል ሀገራዊ ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በከተማ ኤክስቴንሽን ትምህርት በማዕረግ የተመረቀችው ዘኪያ መሀመድ በበኩሏ ጊዜዋን በአግባቡ መጠቀሟ በትምህርቷ ውጤታማ እንዳደረጋት ተናግራለች። በቀጣይም በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ችግር የተነሳ ጉዳት የሚደርስባቸውን ወገኖች ለመታደግ የሙያው ስነምግባርን አክብራ እንደምትሰራ ተናግራለች። በተለይ በትምህርት በቀሰመችው እውቀት ተጠቅማ የእንቶችንና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚጠበቅባትን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀቷን ገልጻለች፡፡ “ለበሽታ ቅድመ መከላከል ሥራ ትኩረት ሰጥታ በመስራት በድንገተኛ በሽታ ለሕመምና ለሞት የሚዳረጉ ዜጎችን ለመታደግ እንደምትሰራ” የተናገረችው ደግሞ በገጠር ጤና ኤክስቴንሽን ትምህርት ክፍል የማዕረግ ተመራቂ የሆነችው ወጣት ሰላማዊት ኦርቾ ናት። ሆሳዕና ጤና ሳይንሰ ኮሌጅ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ከ9 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሕክምና ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ማስመረቁ ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም