የከተሞች መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ከሙስና የጸዳ እንዲሆን አስፈጻሚ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል

117
ሰኔ 2/2011 የከተሞች መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ከሙስናና ከብክነት በጸዳ መልኩ ህዝቡን የተሻለ ተጠቃሚ እንዲያደርግ አስፈጻሚ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን አሳሰበ። የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በበኩሉ በ859 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሦስተኛውን ዙር የከተሞች መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም በመጪው ዓመት እንደሚጀመር አስታውቋል። የከተሞች መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ሪፓርት አላላክ፣ ቅሬታና አቤቱታ አቀራረብ ላይ ያተኮረና በኮሚሽኑ የተዘጋጀው የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ በዚህ ወቅት እንዳሉት ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄደው ሦስተኛው የመሰረተ ልማት ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆንና ህዝብን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ከሙስናና ከብክነት መከላከል ያስፈልጋል። ሙስናና ብልሹ አሰራር የልማትና የእድገት ጠንቅ መሆኑን አመልክተው፣ በሙስና ለተለያዩ ማህበራዊ ሥራዎች እንዲውል በብድርና በእርዳታ የተገኘ ገንዘብ ጭምር ለምዝበራ እየተጋለጠ መሆኑን ገልጸዋል። “ሙስና በሀገሪቱ ዋነኛ የገንዘብ ማሸሺያ መሆን የውጭ ምንዛሬ እጦት ከማስከተሉም በላይ በሀገሪቱ የልማትና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ ጫና እየፈጠረ ይገኛል” ብለዋል። በመሆኑም ለከተሞች መሰረተ ልማት ግንባታ የተገኘውን ከፍተኛ ገንዘብ በአግባቡ በመቆጣጠርና ለታለመለት ዓላማ በማዋል ህዝቡን ተጠቃሚነት በየደረጋው ማረጋገጥ እንደሚገባ አቶ ወዶ ተናግረዋል። ኮሚሽኑ ዓለም ባንክን ወክሎ ፕሮግራሙ ከሙስናና ብልሹ አሰራር በፀዳ መልኩ እየተተገበረ ስለመሆኑና በፕሮጀክቶች ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በመከታተል በዓመት ሁለት ጊዜ ለባንኩ ሪፖርት በማቅረብ የሚቆጣጠር መሆኑንም አስታውቀዋል። በቀጣይ የሚከናወኑ ሥራዎች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ፕሮግራሙን የመምራት፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት የተጣለባቸው ተቋማት አመራሮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አቶ ወዶ አሳስበዋል። እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በፕሮግራሙ ትግበራ ወቅት ችግር ሲያጋጥም ተገቢና ህጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ ኮሚሽኑ የዘረጋው የመረጃ አያያዝና ሪፖርት አቀራርብን መጠቀምና ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራርን ማስፈን ያስፈልጋል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ተወካይ አቶ አምላኩ አዳሙ በበኩላቸው “ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በ556 ሚሊዮን ዶላር በ44 ከተሞች ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው ዙር የከተሞች መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል” ብለዋል። ፕሮግራሙን በመጪው ዓመት ወደ 117 ከተሞች ለማስፋፋት መታቀዱን ጠቁመው፣ መርሃ ግብሩን ለማስፈጸም የዓለም ባንክ፣ የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲና የኢትዮፕያ መንግስት 859 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መመደባቸውን አስታውቀዋል። እንደተወካዩ ገለጻ የፕሮግራሙ ዋና ዋና ዓላማ የከተሞች የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዲፈቱ ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲፋጠን፣ ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም እንዲገነባ፣ የሥራ እድል ፈጠራ እንዲስፋፋና ከተሞች ለመኖሪያና ለኢንቨስትመንት ምቹና ሳቢ እንዲሆኑ ማድረግ ናቸው። በዚህ በኩል ባለፉት 10 ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች ከፍተኛ መነቃቃትና ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል። አቶ አምላኩ እንዳሉት የከተሞች መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራሙ ያተኮረው በከተሞች የኮብል ድንጋይ ንጣፍ፣ የጠጠር መንገዶች፣ ድልድዮችና የእግረኛ መንገድ ጥገና ሥራዎች ላይ ነው። በተጨማሪም ሕብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና የስልክ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም