የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ችግኝ ተከሉ

60
ሰኔ 2/2011የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በየካ ክፍለ ከተማ ኮተቤ ገብርኤል አካባቢ በሚገኘው በአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የተከለለ ቦታ ላይ በዛሬው ዕለት የችግኝ ተከላ አካሄዱ፡፡ "የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች አንድነት ለአረንጓዴ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የምክር ቤቱ አባላት የችግኝ ተከላውን ያካሄዱት። የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ላክዴር ላክባክ የችግኝ ተከላው አላማ አካባቢን ማልማትና መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በሰው ልብ ውስጥ ፍቅርና ሰላም መትከል እንደሚገባ መልዕክት ለማስተላለፍ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል። ''ችግኙን መትከል ማለት በውስጣችን ሰላምና ፍቅር መትከል እንደሆነና ሁሉም በውስጡ ሰላሙንና ፍቅሩን ከተከለ አሁን በብዛት የሚታየው ግጭት እና ያለመረጋጋት ጉዳዮች ማስቀረት ይቻላል'' ብለዋል። ችግኝ መትከል በራሱ ግብ እንዳልሆነ ያመለቱት አቶ ላክዴር ችግኞቹ እስኪጸድቁና የሚፈለገውን ጥቅም እስኪሰጡ ድረስ በሚመለከተው አካል በአግባቡ ሊጠበቁናና እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ''ችግኙ ተተክሎ እንክብካቤ ካልተደረገለት እንደሚደርቀው ሁሉ አንድነታችንን ሰላማችንና ፍቅራችንን መንከባከብ እና መጠበቅ ካልቻልን የሚፈለገውን ነገር ማምጣት እንደማይቻል መገንዘብ ሁሉም ዜጋ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት መወጣት ይገባዋል'' ብለዋል። ሌላዋ የምክር ቤቱ አባልና የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ህይወት ሃይሉ በበኩላቸው የችግኝ ተከላው በአገር አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመፍታት እየተሰራ ያለውን ስራ የሚያስተዋውቅ እንደሆነ ገልጸዋል። የምክር ቤቱ አባላት ያደረጉት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ተከሎ የሚመጣ ችግር ለመፍታት ርምጃ መጀመሯን የሚያመላክት እንደሆነ ተናግረዋል። ከባለፉት ዓመታት በላቀ ደረጃ እያንዳንዱን የህብረተሰብ ክፍል ባሳተፈ መልኩ በአገር አቀፍ ደረጃ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት የ4 ቢሊዮን የዛፍ ችግኝ የመትክል የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር በአገሪቷ ከፍተኛ ንቅናቄ እንደፈጠረና ይሄንንም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊደግፈው እንደሚገባም አመልክተዋል። በመጪው ክረምት አራት ቢሊዮን የሚደርስ የዛፍ ችግኝ በመላ አገሪቱ ለመትከል የሚያስችል የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር ወጥቶ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት በይፋ ተጀምሯል። መርሃ ግብሩ መጀመሩን ተከትሎ የተለያዩ አካላት የችግኝ ተከላ አከናውነዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም