የፌዴራል መንግስት በጀት ከ386 ቢሊዮን 954 ሚሊዮን ብር በላይ ሆኖ ተወሰነ

118
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2011 የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 71ኛ መደበኛ ስብሰባው የ2012 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት በጀት ረቂቅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል። ምክር ቤቱ በቀጣዩ በጀት ዓመት ለሚከናወኑ ስራዎችና አገልግሎቶች 386 ቢሊዮን 954 ሚሊዮን 965 ሺህ 289 ብር እንዲሆን ውሳኔ በማሳለፍ እንዲጸድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል። ከተመደበው በጀት ለመደበኛ ወጪዎች 109 ቢሊዮን፣ ለካፒታል ወጪዎች 130 ቢሊዮን፣ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 140 ቢሊዮን እንዲሁም ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ስድስት ቢሊዮን ብር እንዲሆን መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። በመጠናቀቅ ላይ ያለው በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት በጀት 346 ቢሊዮን 915 ሚሊዮን 451 ሺህ 948  ብር እንደነበር  ይታወቃል። ከዚህ ውስጥ ለመደበኛ ወጪ 91 ቢሊዮን 67 ሚሊዮን 160 ሺህ 588 ብር እንዲሁም ለካፒታል ወጪ 113 ቢሊዮን 635 ሚሊዮን 559 ሺህ 980 ብር ተመድቦም ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም