የግል ትምህርት ቤቶች ሁለንተናዊ ስብዕና ያለው ትውልድ በመፍጠር ሂደት ሚናቸው ሊጠናከር ይገባል ተባለ

69
ሰኔ 1 ቀን 2011 ሁለንተናዊ ስብዕና ያለው ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የግል ትምህርት ቤቶች የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጠየቀ። የትምህርት ልማትን በማጎልበት ሁለንተናዊ ስብዕና ያለው ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የግል ትምህርት ቤቶች ሚናቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ገለጸ። በትምህርት መስክ ከሚሰራው ኤዱቬት አዲስ ለመጀመሪያው ጊዜ የተዘጋጀው የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች አውደ ርዕይ ዛሬ በይፋ ተከፍቷል። የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት እንደገለጹት ለትምህርት ተደራሽነት በሚደረገው እንቅስቃሴ የግል ትምህርት ቤቶች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ ይገኛሉ። የትምህርት ስራ በአንድ ተቋምና በተወሰኑ ግለሰቦች የሚሰራ ሳይሆን የወላጅ፣ የትምህርት ቤቶች፣ የመንግስትና የህብረተሰቡን ተሳትፎ የሚጠይቅ ተግባር ነው። በመሆኑም በመዲናዋ የግል ትምህርት ቤቶች ሁለንተናዊ ስብዕና ያለው አገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት የሚያደርጉትን አስተዋጾኦ አጠናክርው መቀጠል አለባቸው ብለዋል። በትምህርት ልማት መስክ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እንደሚያስችል ጠቁመው ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ከግል ትምህርት ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ ነው ብለዋል። የኤዱቬት አዲስ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ብሌን ምስክር እንደተናገሩት ትምህርት ለሰው ልጅ ያለውን ጠቀሜታ በመረዳትና ፍሬያማ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር የግል ትምህር ቤቶች ሚና ቀላል አይደለም። የአውደ ርዕዩ ዋና ዓላማም ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ብቻ ሳይሆን ለልጆቻቸው ጥራት ያለው ትምህርት የሚሰጥበትን ተቋም እንዲለዩና ተቀራርበው እንዲሰሩ ለማስቻል መሆኑን ጠቁመዋል። በፕሮግራሙ በሚደረጉ ውይይቶችያሉትን ክፍተቶች ለይቶ መንግስትም ድጋፍ የሚያደርግበትን ሁኔታ ለማመላከት መሆኑንም አክለዋል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው አውደ ርፅይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶችና የተለያዩ የንግድ ኩባንያዎች ተሳታፊ ሲሆኑ ነፃ የአይን ምርመራ እንደሚካሄድም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም