የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል ተተኪው ትውልድ የአካባቢ ጥበቃ እንዲያደርግ መሥራት ያስፈልጋል-ኮሚሽኑ

114
አዳማ/ሶዶ ሰኔ 1 ቀን 2011 የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል ተተኪው ትውልድ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ሊሰጥ ይገል የደን አካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ። የዓለም አካባቢ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ46ኛ ጊዜ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ''የአየር ብክለትን በጋራ እንከላከል!'' በሚል መሪ ቃል ተከብሯል። የደን አካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ፍሬኔሽ መኩሪያ በበዓሉ ላይ እንዳሳሰቡት አረንጓዴ ልማት ባህል ሆኖ እንዲቀጥል መሥራት ያስፈልጋል። የአካባቢና ሥነ ምህዳር መራቆት ከቤትና ኢንዱስትሪዎች የሚወጣ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ፣የአገልግሎትና ትራንስፖርቴሽን ዘርፍ የካርበን ልቀት የአየር ንብረትን እየተፈታተኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለማቃለል ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ የሚገኙ ተማሪዎች በአካባቢ ፅዳትና ውበት፣በደን ልማትና ችግኝ ተከላ፣በታዳሽ ኃይሉ አጠቃቀም ዙሪያ ግንዛቤያቸው እንዲጎለብት ማድረግ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል። ''ለነገው ትውልድ የምናስረክባት አገር ፅዱ፣ውብና ለዜጎች ጤንነት የተሰማማ የአየር ፀባይ እንዲኖራት ለማድረግ ከዘመቻ የተላቀቀ የአረንጓዴ ልማት ሥራ ባህል አድርገን ማስቀጠል አለብን'' ብለዋል። የኦሮሚያ የደን፣ አካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦና ያዴሳ በበኩላቸው የትምህርት ተቋማት፣  የወጣቶችና የሴቶች አደረጃጀቶች በአረንጓዴ ልማት እንዲስፋፋ መሥራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል ፡፡ በክልሉ በክረምት ወራት ከ3 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል መታቀዱንም አስታውቀዋል። ከቤት ውስጥ በሚወጣ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ በሚያስከትለው የአካባቢ ብክለት እየተጎዱ ካሉት 10 አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚ መሆኗን የገለጹት አቶ ቦና፣ይህንን ገፅታ ለመቀየር ለልማት ስትራቴጂው ውጤታማነት መረባረብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው በበኩላቸው ከተማዋየቤት ውስጥ ቆሻሻ በሚያስከትለው የአካባቢ ብክለት እየተጠቁ ካሉት የአገሪቱ ከተሞች አንዷ መሆኗን ገልጸው፣ችግሩን ለመቀልበስ ለፅዳትና ውበት ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል። ከከተማዋ የሚወጣውን ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመለወጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑንና በቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ ዘመናዊ አሰራር በመዘርጋት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ በወላይታ ዞን የአካባቢ ጥበቃ ቀንን ምክንያት በማድረግ በወላይታ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ተጀምሯል፡፡ ዘመቻውን በይፋ የከፈቱት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ ከመንደር እስከ ዞን በተዋቀረው የአረንጓዴ ልማት በመሳተፍ   አረንጓዴ ወላይታን ለመፍጠር ነዋሪዉ ተሳትፎዉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡ የዞኑ አከባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘለቀ ዛራ በበኩላቸው በዚህ ዓመት ሁሉም ቀበሌዎች የማህበረሰብ ንቅናቄ በማድረግ እያንዳንዱ ነዋሪ 40 የደን ችግኝ እንደሚተክሉ አስታውቀዋል፡፡ አሁን ላይ ከ98 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውንና ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው፣ለግንባታ አገልግሎትና ለአካባቢ ጥበቃ የሚውሉ ዝርያዎች እንደሚተከሉ ገልጸዋል፡፡ በዞኑ የአዴ ኮይሻ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አባይነህ አንጁሎ ባለፈው ዓመት በልማት ቡድኖች በመደራጀት ለተከሏቸው ከ500 በላይ ችግኞች እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም በአካባቢያቸዉ ነፋሻማ አየር እንዲኖር ከማድረግ ባለፈ፤ አካባቢው እንዲጠበቅ በመደረጉ የአፈር ለምነት እየተመለሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዘንድሮም ከአንድሺህ በላይ ችግኞች ለመትከልና ለመንከባከብ መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም