በደቡብ ክልል በመኽር እርሻ ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ይሸፈናል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል በመኽር እርሻ ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ይሸፈናል
60
ሰኔ 1/2011በደቡብ ክልል በተያዘው የምርት ዘመን በመኽር እርሻ ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር እንደሚሸፈን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በመኽር እርሻ በዘር ከሚሸፈነው 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከ75 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል። ለመኽር እርሻው ዝግጅት እንዲረዳም ለ11 ሺህ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች የክህሎት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንና ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ የመኽር እርሻ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች የአርሶ አደር ስልጠና እንደሚጀመርም ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ለመኽር እርሻ ሥራ የሚሆን 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርጥ ዘርና የአፈር ማደበሪያ መሰራጨቱንና ከዚህ ውስጥ 100 ሺህ ኩንታሉ የስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ ሩዝና ሌሎች ሰብሎች መሆናቸውን ገልጸዋል። በዋና ዋና ሰብሎችና በስራስር ፍራፍሬና የጓሮ አትክልቶች ከሚለማው 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ይገኛል ተብሎ ከሚጠበቀው 75 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ውስጥ 35 ሚሊዮን የሚሆነው የስንዴ፣ ገብስ ፣ ጤፍና ሌሎች ሰብሎች ሲሆኑ ቀሪው በስራስር፣ ፍራፍሬና የጓሮ አትክልት የሚሸፈን መሆኑን ጠቁመዋል። የዝናብ መቆራረጥ ችግር እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች ከመጠን በላይ ዝናብ ሊኖር ይችላል ተብሎ እንደሚጠበቅና ከመቆራረጡ ጋር በተያያዘ የስንዴ ዋግ በሽታ ክስተት እንደሚያጋጥም ተናግረዋል።ለዚህም አርሶ አደሩ የዋግ መከላከያ ኬሚካል አስቀድሞ እንዲያዘጋጅ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ አንደሚሰራ አመልክተዋል። በክልሉ በበልግ እርሻ ይለማል ተብሎ በዕቅድ ከተያዘው 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 845 ሺህ ሄክታሩ በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑንም አቶ ዳንኤል ጠቁመዋል።