ነዋሪዎች መንግሥት ሕገ ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ለመከላከል ቁርጠኛ እንዲሆን ጠየቁ

58
ጅማ ሰኔ 1/ 2011 መንግሥት ሕገ ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ለመከላከል ቁርጠኛ እንዲሆን  የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ። ''ጅማን ከሕገ ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ እንከላከል!'' በሚል መሪ ሐሳብ ትናንት ሕዝባዊ ውይይት በከተማዋ ተካሂዷል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ሱልጣን አባ መጫ በሠጡት አስተያየት ሕገ ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ የተስፋፋው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ባለሥልጣናት በመደገፉ  ነው ብለዋል። ባለሥልጣናቱ ኃላፊነታቸው ባለመወጣታቸው ውድ የሆነውን የተፈጥሮ ሀብት ለወረራ ያጋለጡ አካላት ቀዳሚ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ይህም ''ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል'' ዓይነት ከንቱ አስተሳሰብን ለማስወገድ እንደሚያግዝ አንስተዋል። ሼኸ ጧሊብ ረሻድ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ሕገ ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ እንዲስፋፋ ያደረገው አካልና ምክንያት ለይቶ ማወቅ እንደሚያስፈልግና ''ትክክለኛና ዘላቂ መፍትሄ'' ለመስጠት ያስችላል ብለዋል። መንግሥትም ሕጋዊነት ለማስከበርና ለመቆጣጠር ቁርጠኛ አቋም  እንዲይዝም አሳስበዋል። የጅማ ከተማ የመሬት አስተዳደርና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከማል ቱሬ በከተማው የተስፋፋውን ሕገ ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ለመከላከል ጥረት ቢደረግም፤ ችግሩን መፍታት ሳይቻል መቆየቱን አምነዋል። መንግሥት ችግሩን  ከግምት በማስገባት መሬትን በቁጠባና በዕቅድ ለመምራት ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል። ኅብረተሰቡም በአዲስ መንፈስ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ በመከላከል ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም