በድጎማ የሚቀርቡ ሸቀጦች በቁጥጥር ማነስ ለኪራይ ሰብሳቢነት እየተጋለጡ ነው

74
ሰኔ 1/2011 ገበያን ለማረጋጋት በመንግስት ድጎማ ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ሸቀጦች በቁጥጥርና ክትትል ማነስ ለኪራይ ሰብሳቢነት እየተጋለጡ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ከክልልና ከተማ አስተዳደር ባለድርሻ አካላትና ተጠሪ ተቋማት ጋር የ2011 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በአዳማ ከተማ መገምገም ጀምሯል። በሚኒስቴሩ የዕቅድና ክትትል ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ህሉፍ በእዚህ ወቅት እንዳስታወቁት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት ፍትሃዊ ድልድልና ተደራሽነትን መሠረት በማድረግ የተለያዩ ሸቀጦች ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተሰራጭተዋል። በዚህ ዓመት ገበያውን ለማረጋጋት በመንግስት ድጎማ ከተሰራጩት ምርቶች መካከል 297 ሚሊዮን ሊትር ፓልም የምግብ ዘይት እንደሚገኝበትና ይህም የዕቅዱን 82 ነጥብ 8 በመቶ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል። በተጨማሪም ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳርና ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ለተጠቃሚው መሰራጨቱን ነው የገለጹት፡፡ ይሁን እንጂ በመንግስት ድጋፍ ለህብረተሰቡ እየቀረበ ያለው ምርት በየደረጃው ባለው መዋቅር የቁጥጥርና ክትትል ሥራ መላላት ለኪራይ ሰብሳቢነት አየተጋለጠ መሆኑን አመልክተዋል። አቶ መንግስቱ እንዳሉት በተለይ የግዢና የጨረታ ሂደት መጓተት፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና ከስርጭት ጋር በተያያዘ የተስተዋሉ ችግሮች የሚጠቀሱ ናቸው። ከእዚህ በተጨማሪ የሸቀጣ ሸቀጡ ምርት ለብልሹ አሰራርና ለሕገ-ወጥ ንግድ የተጋለጠ በመሆኑ ህብረተሰቡን በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ ማድረግ አለመቻሉን አመልክተዋል። በተያያዘ ባለፉት ዘጠኝ ወራት አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ የወጣላቸው የገቢ ምርቶች ላይ ሚኒስቴሩ የጥራት ቁጥጥር ለማድረግ መንቀሳቀሱን አቶ መንግስቱ ተናግረዋል። “ በእዚህም አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ የወጣላቸው 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የገቢ ምርቶች ላይ የቁጥጥር ሥራ በማከናወን ፈቃድ ሰጥቷል” ብለዋል፡፡ በተደረገው የቁጥጥር ሥራም ከደረጃ በታች የሆኑ የተለያየ መጠን ያላቸው ኤሌክትሮድ፣ ጥቅል የኤሌክትሪክ ገመድ፣ የኃይል ቆጣቢ አምፖሎች፣ ብስኩቶችና መጠጦች እንዲሁም የቆርቆሮ መስሪያ ጥሬ ዕቃ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ መታገዱን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም የህብረተሰቡን ጤና፣ ደህንነትና ጥቅም እንዳይጎዳ ቢደረግም በኮንትሮባንድና በህገ-ወጥ ንግድ አማካኝነት ወደ ገበያ የሚገቡ የአስገዳጅ ደረጃ ምርቶች በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን አቶ ምንግስቱ አስረድተዋል። “እስከ ሦስተኛው ሩብ በጀት ዓመት በፌደራል ደረጃ ለ82 ሺህ 501 የተለያዩ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቶችን ለመስጠት ታቅዶ ከዕቅድ በላይ 112 በመቶ ማከናወን ተችሏል” ብለዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን የማምረት አቅም፣ የምርት ጥራትና ምርታማነትን ማሳደግ የበጀት ዓመቱ ሌላው የትኩረት መስክ ነው። እንዲሁም ቀልጣፋና የላቀ የገበያ ትስስር ስርዓት በመገንባት የውጪ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ፣ ለአካባቢ ተስማሚ የሆነ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ባለፉት ወራት ትኩረት የተሰጠባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አስረድተዋል። የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አገኘው ተሻገር በበኩላቸው ንግድና ገበያ ልማት በክልሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የላቀ ሚና የሚጫወትበትን ስርአት እውን ለማድረግ ቢሮው ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም