በክልሉ 40 ሚሊዮን ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል

98
አሶሳ  ሰኔ  1/ 2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በክረምት ከ40 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸው የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። ተከላው በካማሽ ዞን አይከናወንም ተብሏል ። የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ወየሳ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ የዘንድሮው ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በያዝነው ወር አጋማሽ ይጀመራል፡፡ ከችግኞቹ 30 ሚሊዮን  ቀርከሃን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢው የዛፍ ችግኞች ናቸው፡፡ ቀሪ 10 ሚሊዮን ችግኞች ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያስገኙ የማንጎ፣ ቡና፣ አቮካዶ ሌሎች የተክል ዝርያዎች እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ችግኝ ተከላው በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት በተራቆተ ከ16 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡ በተጓዳኝ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ተከታታይ እንክብካቤ በማድረግ ችግኞቹ ለማጽደቅ እንደሚሰራ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡ መርሐ ግብሩ  አገራዊ የአረንጓዴ ልማት እቅድን መሠረት አድርጎ እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡ በክልሉ ችግኞቹ የሚተከሉት በአሶሳና መተከል ዞኖች ሲሆን፣በካማሽ ዞን በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ተከላ እንደማይከናወን ተናግረዋል፡፡ የአሶሳ አረንጓዴ ችግኝ ሽያጭ ማህበር አካባቢውን የተፈጥሮ ውበት የመጠበቅ ዓላማ በማድረግ በዚህ ዓመትም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ችግኞችን ማዘጋጀታቸውን የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ብርትኳን ታደሰ ገልጸዋል፡፡ ማህበሩ ከ2006 ጀምሮ በየዓመቱ ችግኞችን ለሽያጭ እያቀረበ እንደሚገኝና ከጤና አዳም እስከ ትላልቅ አገር በቀል ዛፎችን እንደሚያቀርብ አስረድተዋል፡፡ በተለይ በክረምት ወራት ግለሰቦች፣ የመንግሥት ተቋማትና የንግድ ድርጅቶች ዋነኛ ደንበኞቻቸው እንደሆኑ ገልጸው፣ ማህበሩ ለአካባቢው ተፈጥሮ ሃብት ልማት አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡ ወይዘሮ አመልሄር መሐመድ የተባሉ ነዋሪ እንደሚሉት በዘንድሮው ክረምት አንድ ሰው 40 ችግኞችን እንዲተክል የተያዘው እቅድ አገሪቱ ከደረሰባት የደን መመናመን አንጻር ተገቢ ነው፡፡ ችግኝ ተከላና እንክብካቤ በአብዛኛው የግብርና ቢሮ ኃላፊነት አድርጎ መመልከት እንደሚታይና ግለሰቦች ችግኞችን በመንከባበከብና በማጽደቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም