በቋንቋው የተጻፉ አገር በቀል ዕውቀቶችን ለመጠቀም በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ማካተት ይገባል-ምሁራን

118
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2010 የግእዝ ቋንቋ የያዛቸውን ዕውቀቶች ለመጠቀምና ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ቋንቋውን በስርዓተ ትምህርት አካቶ ማስተማር እንደሚገባ ተገለፀ። ከሰሞኑ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሲካሄድ በነበረው አራተኛው አገር አቀፍ የግእዝ ጉባኤ በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡበትና የወደፊት ይሁንታዎች የተጠቀሱበት ነበር። ግእዝና ኢትዮጵያ፣ የአገር በቀል ዕውቀቶች ልማታዊ ፋይዳ፣ የግዕዝ ፊደላትና ፍካሬ ክዋከብት፣ የግእዝ ቁጥሮች፣ የቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ ክዋኔ ጥበባት ለአገራችን ትያትር ዕድገት ያለው ግብዓት፣ የግእዝ ቋንቋ ጥናት ትውፊቱና ትንቢቱ በዓውደ ጥናቱ ከቀረቡ ጥናቶች መካከል ናቸው። የግእዝ ቋንቋ ከቅድመ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ በኢትዮጵያ የተነገረ፣ ለብዙ ዘመናት የጽህፈትና የቤተ መንግስት የስራ ቋንቋነት ያገለገለ፤ የራሱ ስርዓተ ጽህፈት ባለቤት የሆነ ብቸኛው አፍሪካዊ አገር በቀል ቋንቋ እንደሆነ ተጠቅሷል። "ኢትዮጵያ ሲባል ህዝቦቿ ናቸው፤ እነዚህ ህዝቦች ደግሞ በዚህ ቋንቋ የጋራ ታሪካቸውን አስፍረዋል፤ ለብዙ ሺ ዘመናት ተግባብተውበታል፤ ጽፈውበታል፣ አዚመውበታል፤ በጥቅሉ አገር ገንብተውበታል" የሚሉት በቅደስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የግእዝ ቀንቋ መምህር ዘርኣዳዊት አድሃና ናቸው። "ግእዝና ኢትዮጵያ" በሚል ርዕስ ጥናታቸውን ያቀረቡት መምህርት ዘርዓዳዊት፤ ኢትዮጵያና ግእዝ ቋንቋ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሃይማኖታዊና መንግስታዊ መስኮች በየትኛውም ጊዜ የተሳሰሩ እንደሆነ ያነሳሉ። "ሌሎች ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎችን ቀድሞ መጻፊያ፣ ማዜሚያ፣ መድረሻ የነበረ ግእዝ ቋንቋ  ነበር" ያሉት አጥኚው፤ "ቋንቋው ለተሰወነ ህዝብና ሃይማኖት ብቻ ተደርጎ መወሰድ የሌለበት ልሳን እንደሆነም" አብራርተዋል። ዛሬ ላይ ቋንቋውን ለውስን ሕብረተሰብና ኃይማኖት ብቻ አድርጎ የማየትና በቸልተኝነት ምክንያት ግእዝ በብዙ መልኩ መዳከሙን አንስተው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ቋንቋውን አሳድጋ ለዘመናት የተጠቀመችበት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት ነው ብለዋል። አዲሱ ትውልድ ወደፊት ጥሩ ካልሆነ አዝማሚያና ከጨለመ አመለካከት በመውጣት በየዓለማቱ አብያተ መጻሕፍት ተሰግስገው የሚገኙ በቋንቋው የተደረሱ አያሌ ድርሳናትና ምስጢራት ለማወቅ የግእዝ ቋንቋ ማጥናት አንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። በዲላ ዩኒቨርሲቲ የአገረሰብ ዕውቀቶች ጥናት ተቋም ዳይሬክተርና ተመራማሪ አቶ አዲሱ ዘገዬ የአገር በቀል ዕውቀቶችና ልማታዊ ፋይዳዎች በሚል ባቀረቡት ጥናት፤ አገር በቀል ዕውቀቶች በህክምና፣ በተፈጥሮ ጥበቃ፣ በግብርና ስራ ዘዴ፣ በአገረሰባዊ ቴክኖሎጂዎች ወይም ዕደ ጥበባት፣ የማይዳሰሱ ርዕዮተ ዓለማትና በሌሎች ዘርፎች በርካታ አገረሰባዊ ዕውቀቶች በግእዝ መጽሐፍትና ድርሳናት እንደሚገኙ ይገልጻሉ። ስለሆነም በግእዝ ቋንቋ የተደረሱ እነዚህን ዕምቅ አገረሰባዊ ዕውቀቶችና ጽንሰ ሃሳቦች በማውጣት ለአገር ልማት ማዋልና ይበልጥ መመራመር፣ በቁጭት መቆፈር እንደሚገባ ነው የተናገሩት። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነ ጽሁፍ መምህሩ አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ የቅኔ፣ ለባህል መድሃኒት፣ ለፍልስፍና፣ ስነ ፈለግ፣ ስዕል፣ ዜማ፣ ቁጥር፣ ስነ ምግባርና ስነ መለኮት ጥበባት ለዘመናዊ ትምህርቶች ግብዓት መጠቀምና ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ አብራርተዋል። ቀንቋው በብቸኝነት በሚነገርባት በቤተ ክርስቲያን ሳይቀር መዳከሙን የሚገልጹት አቶ ይኩኖአምላክ፤ ቋንቋው የያዛቸውን አገር በቀል ዕውቀቶችና ጥበባት ለመጠቀም በስርዓተ ትምህርቱ ማካተትና በንባብ ስልት መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል። በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቅዱስ ያሬድ ጥንታዊ ስነ ጽሁፍና ብራና ጥናቶች ማዕከል መምህሩ ዶክተር ሐጎስ አብርሃ "ገና ምዕራባዊያን ሳይጀምሩት ኢትዮጵያ ፍካሬ ክዋከብት ባለቤት እንደነበረች በጥናት ተረጋግጧል" ይላሉ። "በአፍሪካ በሕይወት ያለ ብቸኛው ፊደል ነው ግእዝ" የሚሉት ዶክተር ሐጎስ፤ እያንዳንዱ 182 የግእዝ ፊደላት የራሳቸው የፍካሬ ክዋከብት ትንተና የሚያገለገሉ ኮድ፣ ቁጥርና ድምጽ እንዳላቸው አውስተዋል። አማርኛ፣ ትግሬኛ፣ ጉራጊኛን ጨምሮ ለበርካታ አገርኛ ቋንቋዎች የጽህፈት ፊደል ማበረከቱን ገልጸው፤ የግእዝ ቀንቋ  መልሶ እንዲያንሰራራ ያሉትን የቋንቋውን ትውፊትና እሴቱን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ነው ያብራሩት። ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው አገር አቀፍ የግዕዝ ጉባኤ ከዚህ በፊት በአክሱም፣ ባሕር ዳርና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ተካሄዷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም