የውሃ አቅርቦቱ በቂ ባለመሆኑ የህክምና አገልግሎቱን እያስተጓጎለ ነው-ሆስፒታሎች

72
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2010 የውሃ አቅርቦቱ በቂ ባለመሆኑ የህክምና አገልግሎት አሰጣጡን እያስተጓጎለ ነው ሲሉ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆስፒታሎች ገለጹ። የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የጉለሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ሆስፒታሎቹ የውሃ ፍጆታቸውን ጉድጓድ አስቆፍረው እንዲጠቀሙ ቢነገራቸውም ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ችግሩን መቅረፍ አልተቻለም ብሏል። በመዲናዋ የውሃ አቅርቦት በቂ አለመሆን የነዋሪዎች አንገብጋቢ ጥያቄ ከሆነ ሰነባብቷል። የችግሩ ስፋት ከነዋሪዎች አልፎም የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ የህክምና ተቋማትንም ጭምር እያዳረሰ ነው። የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገረቻቸው የጤና ተቋማትም የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን ይገልጻሉ። በህክምና ተቋማት የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ውሃ ከህክምና መሳሪያዎችና ከመድሃኒቶች ባልተናነሰ መልኩ ለአገልግሎቱ ጥራት ያለው አስተዋጽኦ የጎላ ነው ሲሉም ይደመጣሉ። የኢዜአ ሪፖርተር በየካቲት 12 እና በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይድ ሆስፒታል የውሃ አቅርቦት ችግር ሥራቸው ላይ ምን ያህል ጫና እየፈጠረ ነው የሚለውን ለማረጋገጥ ቅኝት አድርጋለች። ሆስፒታሎቹ የህክምና መሳሪያ፣ የአልጋና የመድሃኒቶች ግብዓት  የተሟላባቸው ቢሆንም በውሃ እጥረት ምክንያት ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸውን ነው ባደረግነው ግኝት ማረጋገጥ የተቻለው። የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይድ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ያዕቆብ አሰማኸኝ እንዳሉት፤ በተቋሙ የህክምና ባለሙያ፣ የህክምና መሳሪያና የመድሃኒቶች ግብዓት የተሟላ ቢሆንም የውሃ አቅርቦቱ በቂ ባለመሆኑ የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠት አልተቻለም። በችግሩ ምክንያት ሆስፒታሉ  የቀዶ ህክምናዎችን በወቅቱ ለታካሚዎች መስጠት ባለመቻሉ ታካሚዎች ለእንግልት እየተዳረጉ  መሆኑን ነው የሚገልጹት። ችግሩን ለመቅረፍ የውሃ ጉድጓድ እንዲቆፈርና ተቋሙ የራሱ ውሃ እንዲኖረው ለማድረግ የተካሄደው ጥናትም "በግቢው የሚመነጨው የአይረን ውሃ በመሆኑ ለህክምና አይውልም " ነው ያሉት አቶ ያዕቆብ። ሆስፒታሉ ከ300 ሺህ ሊትር በላይ የሚይዝ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር ያዘጋጀ ቢሆንም አቅርቦቱ ዝቅተኛ በመሆኑ የህክምና አገልግሎቱ ላይ ጫና ማሳደሩንም አክለዋል። የየካቲት 12 ሆስፒታል ህክምና ስፔሻሊስትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል አበበ በበኩላቸው "የችግሩ አሳሳቢነት ግንዛቤ ውስጥ አልገባም፤ ምላሽ መስጠት ያለባቸው አካላት በቂ ምላሽ እየሰጡ አይደለም’’ ብለዋል። በተለይም ሆስፒታሎች ላይ የውሃ አቅርቦቱ በልዩ ሁኔታ መታሰብ ያለበት ጉዳይ መሆኑ ለሚመለከታቸው አካላት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም ምላሹ በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን ሃላፊው አንስተዋል። ይህም በህክምና አገልግሎቱ ላይ ጫና እያሳደረና የህክምና ባለሙያዎችንና ታካሚዎችን እያማረረ ነው ይላሉ። የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የጉለሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በበኩሉ አካባቢው ላይ ያለው የውሃ አቅርቦትና የነዋሪዎች አሰፋፈር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ የውሃ አቅርቦቱ ከሌሎች የመዲናዋ አካባቢዎች በተለየ መልኩ ችግሩ በስፋት አለ ብሏል። ይህም ደግሞ ከአካባቢው ነዋሪዎች ባለፈም ሆስፒታሎቹ ለውሃ ችግር ተጋላጭ እንዲሆኑ ምክንያት መሆኑንም ጠቁመዋል። በጽህፈት ቤቱ የደንበኞች የውሃ አገልግሎት ንዑስ የስራ ሂደት አቶ ክፍሌ አበበ እንደተናገሩት ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት ውሃው በፈረቃ እንዲዳረስ በማድረግና በቦቴ በማመላለስ አቅርቦቱ ተደራሽ እየተደረገ ቢሆንም በቂ አይደለም ብለዋል። ይሁን እንጂ  ትላልቅ ተቋማት የውሃ ፍላጎታቸውን በራሳቸው እንዲያሟሉ ለማድረግ በግቢያቸው ውስጥ የውሃ ጉድጓዶችን እንዲያስቆፍሩ በተነገራቸው መሰረት ቢያስቆፍሩም ጉድጓዱን ጥቅም ላይ እያዋሉት አይደለም ብለዋል። ጉድጓዶቹ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ከሚያደርጋቸው ነገሮች መካከል የውሃው አይነት ለህክምና የሚውል አለመሆኑና ከተቆፈሩ በኃላ የማጥሪያ ሂደቶችን በሚመለከት አስፈላጊውን እገዛ እየጠየቁ ባለመሆናቸው እንደሆነ ይናገራሉ። በስቆፈሩት የውሃ ጉድጓድ የሚመነጨው ውሃ የአይረን ይዘት ያለው ሲሆን ውሃው ህክምና ተደርጎለት ለአገልግሎት እንዲውል ለማስቻል በተለይም ቴክኒካዊ የሆኑ እገዛዎችን የሚያገኙበት እገዛ ከባለስልጣኑ እየጠየቁ ባለመሆኑ የሚያስቆፍሩት የውሃ ጉድጓዶች  ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አድርጓል ይላሉ። በተጨማሪም የህክምና ተቋማቱ ጉድጓዱን አስቆፍረው በባለስልጣኑ ጋር በመተባበር በፍጥነት ወደ ስራ ካላስገቡ አሁን ባለው የውሃ መጠን ችግሩን መቅረፍ አይቻልም ሲሉ አክለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም