ለሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ውጪ አደራዳሪ የለም - የፖለቲካ ምሁር አዎል አሎ

103
ግንቦት 30/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና መንግሥታቸው "የሱዳን የፖለቲካ ኃይሎችን ለማደራደር ብቁ ናቸው" ሲሉ የፖለቲካ ምሁሩ አዎል አሎ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ከሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ሸንጎ መሪ ሌተና ጄኔራል አብዱል ፈታህ አል-ቡርሀን ጋር ለመነጋገር ሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ናቸው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ  የተመራው የልዑካን ቡድን ከሱዳን የነፃነትና የለውጥ ኃይሎች አባላት ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምን ለማምጣት በቁርጠኝነት እያከናወነች ነው። በአሁኑ ወቅትም በሱዳን የተፈጠረውን ችግር በመፍታት በአገሪቷ ሰላም እንዲሰፍን በትጋት ትሰራለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከሱዳን የነፃነትና የለውጥ ኃይሎች አባላት ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ አልጀዚራ ያነጋገራቸው በኬሌ ዩኒቨርስቲ የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካዊ ጉዳዮች መምህር አዎል አሎ እንደሚሉት፤ የሱዳንን ግጭትን ለማቆም ኢትዮጵያ ሁለቱንም ወገኖች በገለልተኛነት ለማደራደር ብቁ ናት። ''ሦስተኛ ወገን ገለልተኛ አካል ይምጣና ሁለቱን ወገኖች ያደራድራቸው ከተባለ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና ከኢትዮጵያ መንግሥት ውጪ የተሻለ ማንም የለም'' ብለዋል። የፖለቲካ ምሁሩ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት ያላት ከፍተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴና እስከ አሁን ኢትዮጵያ በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ነጻና ገለልተኛ ሆና መቆየቷን በምክንያትነት አንስተዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የድርድር ሂደት ላይ ውስንነት ሊኖር እንደሚችል የገለጹት አዎል አሎ፤ በተለይም ከወታደሩ በኩል በሚመጣ የስምምነት ሀሳብ ላይ ሊያዘነብሉ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። ይሁን እንጂ "ስምምነቱ የአብዮቱን ፍላጎትና ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ሀሳብ ከሚወክለው ከሽግግር መንግሥቱ ፍላጎት ጋር አብሮ መሄድ አለበት" ብለዋል። በሱዳን የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት ሱዳንን ወደ ሰላም እሰክትመለስ ድረስ ከአባልነት አግዷታል። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት በሱዳን የተፈጠረው ቀውስ በአስቸኳይ እልባት ካልተሰጠው በጎረቤት አገሮች ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድር እምነት አለው። ፕሬዝዳንት አልበሽርን ከስልጣን አውርዶ የስልጣን መንበሩን የተቆናጠጠው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ስልጣኑን ለሲቪል መንግስት የሚያስረክብበትን ጊዜ ካላፋጠነ በመላው ሱዳን አዲስ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚጠሩ የአገሪቷ የተቃውሞ መሪዎች በቅርቡ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል። ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር እንደ አውሮጳውያኑ አቆጣጠር ከ1989 ጀምሮ ለ30 ዓመታት አገሪቷን በፕሬዝዳንትነት መምራታቸው ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም