ቻይና ከኢትዮጵያ ጋራ ያላት ግንኙነት ከሁለትዮሽ ግንኙነት የላቀ ነው...በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር

91
ግንቦት 30/2011 ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለሌላው ዓለም ስትራቴጂክ ከመሆኗ አንጻር ቻይና ከኢትዮጵያ ጋራ ያላት ግንኙነት ከሁለትዮሽ ግንኙነት የላቀ ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ተናገሩ። አምባሳደር ታን  ጂአን ትናንት ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋር በትምህርት ዘርፍ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው  ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። አምባሳደር ታንጂአን  በእዚህ ወቅት እንደ ገለጹት ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት እንደሌሎቹ የአፍሪካ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ብቻ እድርጋ አትመለከተውም። ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለተቀረው ዓለም ስትራቴጂክ ቦታ ከመሆኗ አንጻር ቻይና ኢትዮጵያን እንደ ዋና መሸጋገሪያ ድልድይ አድርጋ እንደምትመለከታትም ተናግራዋል። ለዚህም ቻይና ለኢትዮጵያ በምትችለው አቅም ሁሉ ያላትን ልምድ ለማጋራትና ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ እንድትሆን ለማድረግ ተገቢውን እገዛ እንደምታደርግም አምባሳደሩ ገልጸዋል። ቻይና እና ኢትዮጵያ የዓለም ስልጣኔ መነሻ አገራት እንደነበሩ ያስታወሱት አምባሳደሩ፣ “ምንም እንኳ ቻይና ዛሬ የተሻለ ደረጃ ላይ ብትገኝም ሁለቱም አገራት በማደግ ላይ ካለው ዓለም የሚመደቡ ናቸው” ብለዋል። ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ከመሆኗ በተጨማሪ በርካታ የዓለም የስልጣኔ መሰረቶች የሆኑ አሻራዎች ያሏት ድንቅ የአለም ኩራት የሆነች አገር መሆኗንም አመልክተዋል። አገሪቱ  የቀድምት የስልጣኔ ታሪኳን ከማስረዳት ውጪ ስልጣኔዎን ማስቀጠል አለመቻሏንም ነው የተናገሩት። ለዚህ ደግሞ የሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት አለመሰራቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰው ኃይሉን በማልማት በኩል ቻይና የድርሻዋን እየተወጣች መሆኗን ገልጸዋል፡፡ “የኢትዮጵያ እድገት ለቻይና ብልጽግና ጉልሀ አስተዋጾ ስለሚኖረው ኢትዮጵያ ከቻይና የምትሻውን አስፈላጊ ድጋፍ ለማድረግ ቻይና ዝግጁ ናት” ሲሉም አረጋግጠዋል። “አንድ አገር ሦስት አይነት ሃብት ይኖረዋል፤ እነዚህም ገንዘብ፣ ህዝብና የተፈጥሮ ሃብትናቸው፤ ነገር ግን ከሁሉም የሰው ሃብት ይልቃል” ሲሉም አምባሳደሩ ተናግረዋል። “ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 100 ሚሊዮን የሚገመት ህዝብ ያላት አገር በመሆኗ ይህንን ህዝብ ብታሰለጥነው በአጭር ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የማትሰለፍበት ምክንያት አይኖርም” ብለዋል። እንደአምባሳደሩ ገለጻ ቻይና በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዓለም ተወዳዳሪ ሀገሮች ተርታ ልትሰለፍ የቻለችበት ዋነኛ ሚስጥር የሰው ኃይሏን በተሻለ አቅም ማብቃት በመቿሏ ነው። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ከቻይና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር ለመስራት የሚያደርጉትን  ጥረት ቻይናእንደምትደግፈው ተናግረዋል። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለሚጠይቃቸው የስልጠና ዘርፎች የቻይና ዩኒቨርሲቲዎች በሁሉም የትምህርት ዓይነት የትምህርት እድል ለመስጠት ዝግጁመሆናቸውን አምባሳደር ታን  ጂአንጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅትም በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በቻይና ዩኒቨርሲቲዎች እየተከታተሉ መሆናቸውን አብራርተዋል። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ በበኩላቸው ከልምድ አንጻር የቻይና ዩኒቨርሲቲዎች ዘመናት ያሰቆጠሩና በቴክኖሎጂ የመጠቁ በመሆናቸው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሰፊ ድጋፍ እንደሚፈልግ ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ከቻይና ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠንከርም የቻይንኛ ቋንቋን ለተማሪዎች እያስተማረ መሆኑንም አመልክተዋል። የቻይና ዩኒቨርሲቲዎች የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት እድል እየሰጡ መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይ ለአገር  እድገት የሚያግዙ  የትምህርት ዘርፎችን በመቅረጽ ትብብር እንዲያድረጉላቸው ጠይቀዋል። በትምህርት ዘርፉ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ለመምከር በተዘጋጀው በእዚህ መድረክ ላይ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የሥራ ባልደረቦችና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ  አመራሮች ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም